የጆርዳኑ ንጉስ የትራምፕን ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ አልቀበልም አሉ
የጆርዳን አጎራባች በሆነው ዌስትባንክ ጨምሮ ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር እንደማይቀበሉ ተናግረዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/243-104529-img-20250212-094503-875_700x400.jpg)
ትራምፕ ግብጽና ጆርዳን በመጨረሻ ፍልስጤማውያንን ለማስጠለል መስማማታቸው አይቀርም ብለዋል
የጆርዳኑ ንጉስ የትራምፕን ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ አልቀበልም አሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የጆርዳኑ ንጉስ አብዱላህ የጋዛ ፍልስጤማውያንን እንዲያሰፍሩና የአሜሪካን ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ እንዲቀበሉ ጫና ቢያደርጉባቸው ሳይቀበሏቸው ቀርተዋል።
ትራምፕ በኃይትሀውስ ከንጉስ አብዱላህ ጋር ሆነው በሰጡት መግለጫ ነዋሪዎችን በማፈናቀል በጦርነት የወደመችውን ጋዛ "የመካከለኛው ምስራቅ ምርጥ ቦታ"የማድረግ እቅዳቸውን እንደሚገፉበት አመላክተዋል።
ትራምፕ ለ15 ወራት በዘለቀው የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የወደመችው ጋዛ መልሳ ከተገነባች በኋላ ፍልስጤማውያን ወደ ቦታቸው አይመለሱም ማለታቸው የአረብ ሀገራትን አስቅጥቷል።
"እንቆጣጠራታለን፤እንኒዘዋለን። አልምተን ለመካከለኛው ምስራቅ ብዙ የስራ እድል እንፈጥራለን" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ እቅዳቸው በቀጣናው ሰላም ያመጣል ብለዋል።
ንጉስ አብዱላህ ቆይት ብለው እንደናገሩት የጆርዳን አጎራባች በሆነው ዌስትባንክ ጨምሮ ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። "ይህ የአረብ ሀገራት አቋም ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
"ፍልስጤማውያንን ሳናፈናቅል አስከፊ የሆነውን የሰብአዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው የሚለው ለሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።"
የጆርዳኑ አቻቸው ይህን ቢሉም ትራምፕ ግን ግብጽና ጆርዳን በመጨረሻ ፍልስጤማውያንን ለማስጠለል መስማማታቸው አይቀርም ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ከአሜሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው።
የአረብ ሀገራትና የፍልስጤም ባለስልጣናት የፍልስጤማውያንን ከጋዛ ማፈናቀል ተግባር በጽኑ እንደሚቃወሙት ቀደም ሲል ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ግልጽ አድርጠዋል።
የእስራኤል-ሀማስ ተኩስ አቁም ስምምነት አሁን ላይ አደጋው ውስጥ ገብቷል። ትራምፕና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ሀማስ በእጁ ያሉ ሁሉንም ታጋቾች በመጭው ቅዳሜ የማይለቅ ከሆነ ስምምነቱ እንደሚፈርስ ዝተዋል።
ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ 1200 ሰዎችን ከገደለና 250 ሰዎችን ካገተ በኋላ እስራኤል በወሰደችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እስራኤል በጋዛ የዘረ ማጥፋት ፈጽማለች በሚል የቀረበባትን ክስ አስተባብላለች