የትራምፕ የጋዛ እቅድ የአሜሪካን "ጨካኝ ዘራፊነት" ያሳያል - ሰሜን ኮሪያ
ፒዮንግያንግ ባወጣችው መግለጫ "አሜሪካ ከቀን ቅዠቷ ወጥታ የሌሎች ሀገራትን ሉአላዊነት እና ክብር መዳፈሯን ማቆም አለባት" ብላለች
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/273-105318-kim-trump_700x400.jpg)
የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር እስራኤልና አጋሯ አሜሪካ በጋዛው ጦርነት የንጹሃንን ደም ማፍሰስ እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ ጠይቋል
ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን የመጠቅለል እቅድ አወገዘች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኪሲኤንኤ) የትራምፕ እቅድ የዋሽንግተንን "ጨካኝ ዘራፊነት" ያሳየ ነው ብሏል።
እቅዱ የፍልስጤማውያንን ሰላምና ደህንነት የማግኘት የቀጠነ ተስፋ ከናካቴው የሚያጠፋ መሆኑንም ነው ኬሲኤንኤ ያወጣው መግለጫ የሚጠቁመው።
"በአሜሪካ መግለጫ አለማችን አሁን ላይ እንደ ገንፎ ድስት እየፈላች ነው" ሲልም አክሏል።
ፒዮንግያንግ የትራምፕ አስተዳደር የፓናማ ካናል እና ግሪንላንድን ለመጠቅለል እና ስማቸውን "ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮ" እና "ገልፍ ኦፍ አሜሪካ" ለማለት ማቀዱን ተቃውማለች።
"አሜሪካ ከቀን ቅዠቷ ወጥታ የሌሎች ሀገራትን ክብርና ሉአላዊነት መዳፈሯን ማቆም ይኖርባታል" ያለው ኬሲኤንኤ ፥ ዋሽንግተንን በዘራፊነት ከሷል።
ፒዮንግያንግ በብሄራዊ ቴሌቪዥኗ ወቅታዊ አቋሟን ስትገልጽ የትራምፕን ስም በይፋ ከመጠቅስ ተቆጥባለች።
በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ከኪም ጆንግ ኡን ጋር የተገናኙት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከተመለሱ በኋላ ከኪም ጋር የመገናኘት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን ግን ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥተው ሲዘግቡት እንደማይታይ ሬውተርስ አስነብቧል።
በአንጻሩ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጦረኝነት በማንሳት ማብጠልጠላቸውን ተያይዘውታልም ይላል።
ሰሜን ኮሪያ ከ48 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የጋዛ ጦርነት እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርባለች፤ እስራኤልን በዋና ደም አፍሳሽነት አሜሪካን ደግሞ በተባባሪነት ስትከስ መቆየቷም ይታወሳል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመንግስታቱ ድርጅት፣ ከአረብ ሀገራት እና አለማቀፍ የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞው ቢበረታባቸውም ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅዳቸውን ለማስፈጸም ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ትናንት ምሽት ከዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ ዳግማዊ ጋር ሲመክሩም አማን ፍልስጤማውያንን እንድታስጠልል የጠየቁ ሲሆን፥ ንጉሱ ግን እቅዱን አልቀበልም ማለታቸው ተዘግቧል።