የግብጽ ፕሬዝዳንት በጋዛ ጉዳይ ለመምከር ወደ ሳኡዲ አቀኑ
ፕሬዝዳንቱ በሪያድ ቆይታቸው በትራምፕ የጋዛ እቅድ ዙሪያ ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል

የአረብ ሀገራት መሪዎች በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ በመጋቢት ወር መጀመሪያ በካይሮ ይወያያሉ
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ተጓዙ።
የግብጽ ብሄራዊ ቴሌቪዥን የፕሬዝዳንቱ የሪያድ ጉዞ ዋነኛ አለማን ባይጠቅስም በጋዛ ወቅታዊ ጉዳይ ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር እንደሚመክሩ እየተዘገበ ነው።
ካይሮ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር መጨረሻ ይፋ ያደረጉትን ጋዛን የመጠቅለል እቅድ ስትቃወም ቆይታለች።
ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን እንድትቀበል የቀረበላትን ጥያቄም ውድቅ አድርጋለች።
የአብዱልፈታህ አል ሲሲ አስተዳደር ፍልስጤማውያን ሳይፈናቀሉ ጋዛን መልሶ መገንባት የሚያስችል እቅድ እንደሚያቀርብ ማስታወቁም ይታወሳል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የአረብ ሀገራት መሪዎች መክረውበታል የተባለውን አማራጭ እቅድ እስካሁን እንዳልተመለከቱት ትናንት ምሽት መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።
ተመሳሳይ ፍልስጤማውያንን የማስጠለል ጥያቄ የቀረበላት ዮርዳኖስ በንጉስ አብዱላህ ዳግማዊ በኩል እንደማትቀበለው ማሳወቋ አይዘነጋም።
ሳኡዲ አረቢያ ፍልስጤማውያንን ከርስታቸው የማፈናቀል እቅድን እንደማትቀበል ደጋግማ ገልጻለች።
አረብ ኤምሬትስም በአቡ ዳቢ ጉብኝት ላደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እቅዱን እንደምትቃወም በይፋ አስታውቃለች።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በሪያድ ቆይታቸው ከሳኡዲ እና የሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር ከፍተኛ ተቃውሞ በተነሳበት የትራምፕ የጋዛ እቅድ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአረብ ሊግ በፈረንጆቹ መጋቢት 4 2025 በካይሮ በሚያደርገው ጉባኤ የትራምፕን እቅድ የሚተካ እቅድ እንደሚያቀርብ ሬውተርስ ዘግቧል።