የግብጹ ፕሬዝዳንት ዛሬ ካርቱም ገብተዋል፤የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ግጭት አልተፈታም
ከሰሞኑ ካርቱምና ካይሮ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል
ፕሬዘዳንት አል ሲሲ ወደ ሱዳን ያቀኑት ኢትየጵያና ሱዳን በድንበር ምክንያት ግጭት ውስጥ በገቡበት ወቅተ ነው
ፕሬዚዳንቱ ካርቱም ሲደርሱ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ተቀብለዋለቸዋል፡፡
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አል ሳዲቅ አል ማህዲ ከሰሞኑ ፕሬዚዳንቱ ካርቱምን የሚጎበኙት በሁለትዮሽ እና በሌሎች ወቅታዊ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ነው ብለው ነበር፡፡ አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና የሱዳን ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
ከሰሞኑ ካርቱምና ካይሮ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ባሳለፍነው ማክሰኞ ዕለት የሀገራቱ የጦር አመራሮች በካይሮ ስብሰባ ባደረበት ወቅት ወታደራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የትብብር ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አል ሳዲቅም ከግብጹ አቻቸው ሳሚ ሹክሪ እና ከግብጽ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል መሃመድ ፋሪድ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ወደ ካርቱም ያቀኑት ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ውዝግብ ዙሪያ እሰጥ አገባ ውስጥ በገቡበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የድንበር ውዝግብ እስካሁን እልባት ማግኘት አልቻለም፡፡