የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩ “ግጭቶች” የሱዳን እና ግብፅ ድጋፍ እንዳለበት ማረጋገጡን ትናንት ገልጾ ነበር
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ “ግጭቶች” የሱዳን እና ግብፅ ድጋፍ እንደነበረበት መገልጹን ተከትሎ ሱዳን ምላሽ ሰጥታለች፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግድያዎችንና “ግጭቶች” በመገምገም የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ በምክር ቤቱ የተቋቋመው ኮሚቴ ከትግራይ ክልል ውጭ ተፈጥረው በነበሩ “ግጭቶች” የሱዳን እና የግብጽ ድጋፍ እንደነበረበት ማረጋገጡን በትናንትናው እለት ገልጾ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሱዳን ድንበር ላይ ታጣቂዎችን የማሰልጠን እና ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዶች ሲከናወኑ እንደነበርም ኮሚቴው ይፋ አድርጓል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሀገራቸው በሌሎች ሀገራት ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትና በአዲስ አበባ በኩል የቀረበው ቅሬታ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አምባሳደር መንሱር ቦላድ ለአል ዐይን ኒውስ በሰጡት መግለጫ ካርቱም ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት አመጽን የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል፡፡ ሀገራቸው ለሁሉም ነገር ሰላምን ብቻ አንደምታስቀድምና እንደምታምን የገለጹት ቃል አቀባዩ ይህም የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋነኛ መርኋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ካርቱም በሌሎች ሀገሮች ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ አለመግባትን እና መልካም ጉርብትናን እንደምትደግፍ ተናግረዋል፡፡ ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ካርቱም፤ ከአዲስ አበባ ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሕጎችንና ደንቦችን መሠረት ባደረገ መልኩ መፈታት አለበት ብላ ታምናለች ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ “ግጭቶች” የሱዳን እና ግብፅ ድጋፍ እንደነበረበት መግልጹን ተከትሎ እስካሁን ከግብጽ በኩል የተሰጠ ምለሽ የለም፡፡