ግብጽ በጋዛ የአጭር ጊዜ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ሀሳብ አቀረበች
ለአጭር ቀናት በሚደረገው ተኩስ አቁም የተወሰኑ ታጋቾች እና የሀማስ እስረኞች እንዲለቀቁ ተጠይቋል
የግብጹ ፕሬዝዳንት ይህን ሀሳብ ያቀረቡት በትላንትናው እለት በኳታር የጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር እየተካሄደ በሚገኝበት ወቅት ነው
ግብፅ አራት እስራኤላውያንን የሃማስ ታጋቾችን በተወሰኑ የፍልስጤም እስረኞች ለመለወጥ በጋዛ የሁለት ቀን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሀሳብ አቀረበች።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ይህን ያሉት ከአንድ አመት በላይ የዘለቀውን አስከፊውን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር ድጋሚ በተጀመረበት ወቅት ነው፡፡
በኳታር ዶሀ መደረግ የጀመረው አሜሪካ ባቀረበችው የዘለቂ ጦርነት ማቆም ሀሳብ ላይ በሚመክረው ጉባኤ ላይ የሞሳድ እና የሲአይኤ ስለላ ድርጅት ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል፡፡
ሲሲ ከአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቦዩን ጋር በካይሮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን ወደ ዘላቂነት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ድርድሮች በ10 ቀናት ውስጥ ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡
በቀረበው ሀሳብ ዙሪያ ከእስራኤልም ሆነ ከሀማስ ምንም አይነት ምላሽ አልተሰማም፤ ነገር ግን ለድርድር ጥረቱ ቅርብ የሆኑ የፍልስጤም ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ “ሀማስ አዲስ የቀረበውን ሀሳብ ሊቀበለው እንደሚችል እጠብቃለሁ። ነገር ግን የትኛውም ስምምነት ጦርነቱን ማስቆም እና የእስራኤል ወታደሮችን ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ማስውጣት እንዳለበት ያምናል” ብለዋል::
የ43 ሺህ ንጹሀንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለማስቆም ግብጽ ፣ ኳታር እና አሜሪካ አሁንም የድርድር ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡
አደራዳሪዎቹ አሁን እያቀረቡ የሚገኙት የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት አላማም ከበርካታ የድርድር ሙከራዎች በኋላ ያልተሳከውን ዘላቂ ተኩስ አቁም በጊዜያዊነት በመቀየር ወደ ሚፈለገው የጦርነት ማስቆም ሂደት ለመጓዝ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል ጦር በአሁኑ ወቅት ሀማስ ድጋሚ ራሱን እያደራጀበት ነው ባለው ሰሜናዊ ጋዛ ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል። ባለፉት 24 ሰአታትም ከ40 በላይ የቡድኑ ታጣቂዎችን ገድያለሁ ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ የፍልስጤም ንፁሀን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ መሆኑን እና ግጭቱ አለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ መስፈርቶችን ወደ ጎን በማለት እየተካሄደ ነው ብሏል፡፡
እስራኤል ምንም እንኳን በድርድሮቹ እየተሳተፈች ብትገኝም ሀማስ በጋዛ እንደ ወታደራዊ ሃይል እና የአስተዳደር አካል እስካልጠፋ ድረስ ጦርነቱ ማቆም እንደማይችል ጽኑ አቋም መያዟ የሽምግልና ሂደቶቹ ስኬታማነት ላይ ጥላ አጥልቷል፡፡