የኢራን ባለስልጣናት ለእስራኤል ጥቃት እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ሊወስኑ መሆኑን ካሚኒ ተናገሩ
ኢራን እስራኤል ያደረሰችባትን ጥቃት ቀላል ነው ብላ ብታጣጥልም፣ ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ እንደሚያስፈልገው እየገለጸች ነው
እስራኤል በቴህራን ላይ ጥቃት የፈጸመችው በ180 ሚሳይሎች ጥቃት የፈጸመችባትን ኢራንን ለመበቀል ነው
የኢራን ባለስልጣናት ለእስራኤል ጥቃት እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ሊወስኑ መሆኑን ካሚኒ ተናገሩ።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች ከሁለት ቀናት በኋላ ባሰሙት ንግግር የኢራን ባለስልጣናት የኢራንን ኃይል ለእስራኤል ማሳየት እንዳለባቸው በትናንትናው እለት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ከሁለት ቀናት በፊት ጽዮናዊ አገዛዝ የተፈጸመው ሰይጣናዊ ድርጊት መናቅም ሆነ መጋነን የለበትም" ብለዋል ካሚኒ።
ባለፈው ቅዳሜ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይን በመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ጦርነት ያስነሳል ተብሎ የተፈራው ውጥረት እንዳይባባስ ጥሪ ሲያደርጉ፣ ኢራን የእስራኤል ጥቃት ያስከተለው ጉዳት "አነስተኛ ነው" ስትል አጣጥላው ነበር።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ቅዳሜ ማለዳ የእስራኤል አየር ኃይል በቴህራን አቅራቢያ በሚገኙ የሚሳይል ፋብሪካዎች እና ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም በምዕራብ ኢራን በሶስት ዙር ከባድ ጥቃት አድርሷል።
ካሚኒ ኢራን ለእስራኤል ኃይሏን ማሳየት እንዳለባት እና እንዴት ይሁን የሚለው በባለስልጣናት እንደሚወሰን ተናግረዋል።
እስራኤል በቴህራን ላይ ጥቃት የፈጸመችው በ180 ሚሳይሎች ጥቃት የፈጸመችባትን ኢራንን ለመበቀል ነው።
ኢራን ባለፈው ጥቅምት አንድ በእስራኤል ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ቀጥተኛ ጥቃት ያደረሰችው፣ የእስራኤልን የሊባኖስ ወረራ እና የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን ግድያ ለመበቀል ነበር።
ኢራን እስራኤል ያደረሰችባትን ጥቃት ቀላል ነው ብላ ብታጣጥልም፣ ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ እንደሚያስፈልገው እየገለጸች ነው።
የሁለቱ ሀገራት ጥቃት መመላለስ አዙሪት የእስራኤል አጋሯን አሜሪካን እና ኢራንን ወደ ቀጥተኛ ቀጣናዊ ግጭት ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።