ሊደረግ የታሰበው እድሳት የቅርሱን ጥንታዊነት ይቀይረዋል የሚል ዜና አለምአቀፍ ተቃውሞ በማስነሳቱ፣ የግብጽ የቅርስ ባለስልጣናት እቅዱን እንዲገመግሙት አስገድዷቸዋል
ግብጽ አወዛጋቢ የነበረውን የፒራሚድ እድሳት እቅድ ሰረዘች።
ግብጽ በጊዛ ከሚገኙት ሶስቱ ፒራሚዶች ውስጥ 'ፒራሚድ ኦፍ መንካውሬ' የተባለውን ትንሹን ፒራሚድ በጥንታዊ ግራናይት ለማደስ ያቀረበችውን እቅድ መሰረዟን በሀገሪቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር የተቋቋመው ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የጥንታዊ ቅርሶች ጠቅላይ ምክርቤት ዋና ጸኃፊ የሆኑት ሙስጠፋ ዋዚሪ ባለፈው ወር እቅዱ "የክፍለ ዘመኑ ፕሮጀክት" ይሆናል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ነገርግን ሊደረግ የታሰበው እድሳት የቅርሱን ጥንታዊነት ይቀይረዋል የሚል ዜና አለምአቀፍ ተቃውሞ በማስነሳቱ፣ የግብጽ የቅርስ ባለስልጣናት እቅዱን እንዲገመግሙት አስገድዷቸዋል።
የመንካውሬ ፒራሚድ ውጨኛው ክፍል ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በላይምስቶን ሳይሆን በግራናይት እንዲሸፈን ሆኖ ነበር ዲዛይን የወጣላት።
ከ16-18 የሚሆነው ድርብርብ ወይም 'ላየር' ብቻ በግራናይት ከተሸፈነ በኋላ ንጉስ መንካውሬ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2503 በመሞቱ ምክንያት ግንባታው ተቋርጧል።
ለክፍለዘመናት የዘለቀው መሸርሸር እና መናድ ብዙ የግራናይት ድርብርቦች እንዲጠፉ እና እንዲፈረካከሱ አድርጓቸዋል።
ዋዛሪ እነዚህን የረገፉ ግራናይቶችን የመተካቱ እቅድ የወጣው ከአንድ አመት የምርመራ እና የመረጃ ማሰባሰብ ስራ በኋላ ነበር ብሏል።
ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ "የመንካውሬ ፒራሚድ ሪቪው ኮሚቴ በፒራሚዱ ስር መንገድ የዘጉትን እና የተበታተኑትን ግራናይቶች የተመካት እቅድ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል።"
ኮሚቴውን እየመራ ያለው የቀድሞ የጥንታዊ ቅርሶች ሚኒስተር ዛሂ ሀዋዝ እያንዳንዱ ድንጋይ የት እንደነበረ ለመወሰን የማይቻል ነው ብለዋል።
በመተካቱ ሂደት ሲሚንቶ ጥቅም ላይ ስለሚውል ፒራሚዱን ያበላሸዋል ተብሏል።
"አትጨነቁ ማለት እፈልጋለሁ። የጊዛ ፒራሚዶች በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው፤ ምንም አይከሰትባቸው" ሲሉ ሀዋዝ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
"በርካታ ቦታዎች ሰዎች አየደወሉ እና ደብዳቤ አየጻፉልኝ" ነው ያሉት ሀዋዝ "አትጨነቁ ፒራሚዶቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው፣ ማንም አይነካቸው" የሚል መልሰ ሰጥተዋል።