ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ፡ “በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እጅ ለመጠምዘዝ የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ”
ግድቡ በጀመሪያው አመት የውሃ ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዟል
የሀገርን አቋም የሚያስተዋውቁ የዲፕማሲ ስራዎችን በመስራት ማንኛውም ጫና እንደሚመከት ፕሬዘዳንቷ ገልጸዋል
የሀገርን አቋም የሚያስተዋውቁ የዲፕማሲ ስራዎችን በመስራት ማንኛውም ጫና እንደሚመከት ፕሬዘዳንቷ ገልጸዋል
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በምንም አይነት ጫና እና እጅ የመጠምዘዝ ተግባር ወደኋላ እንደማይመለስ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ አምስተኛውን ዙር የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች 6ኛ ዓመት የስራ ዘመንን ዛሬ ሲከፍቱ እንደገለጹት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ እጅ ለመጠምዘዝና ጫና ለማድረግ ሙከራዎች ሲደረጉ ነበር፡፡
በዚህ ዓመት የሚሰሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የሀገርን አቋም የሚያስተዋውቁና ሰፊ ተደራሽነት እንዲኖራቸው እንደሚደረግ ያነሱት ፕሬዘዳንቷ ማንኛውንም ጫና ለመመከት ዝግጅት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ በተሳተፈችባቸው ድርድሮችም ሆነ ቀደም ሲል በነበሩት ድርደሮች ወቅት የተከተለችው መርህ ያውና ተመሳሳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይህም የተፋሰሱን ሀገራት ሳይጎዳ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ነው የምትሻው ብለዋል፡፡ እስካሁን ጥንቃቄ የተሞላበት ድርድር ሲካሄድ መቆየቱንም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አስታውቀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን፣ምሁራንን፣ፖለቲከኞችን፣እና ሌሎችንም በማማከር ሥራዎች መሰራታቸው ያነሱት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ የተደረጉ ውይይቶችም ኢትዮጵያ ልትይዘው የምትችለው አቋም ነጥሮ እንዲወጣ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
ከዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ጋር በተለይም ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ውይይቶች መደረጋቸውንም ፕሬዚዳንቷ አንስተዋል፡፡ በዚህ ዓመት የህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ወደ ማመንጨት እንዲሸጋገሩ ቀደም ብሎ ዕቅድ መያዙ የሚታወቅ ሲሆን ይህም ትኩረት ተደርጎበት የሚሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም ሀምሌ ወር ላይ የተጀመረው የ4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የመጀመሪያ ዙር ሙሌት መከናወኑ የሚታወስ ሲሆን በ2013 ክረምት የሚደረገው ሁለተኛው ዙር ውኃ ሙሌትም በተያዘለት ገዚ እንዲከናወን ይሠራል ብለዋል፡፡