የሦስቱን ሀገራት መሪዎች ድርድሩን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ፕሬዝዳንት ራማፎዛ አድንቀዋል
የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነገ ይቀጥላል
በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል እየተካሔደ የሚገኘው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013ዓ.ም. እንደሚቀጥል የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲርል ራማፎዛ ገለጹ፡፡ ድርድሩ ላለፉት ሰባት ሳምንታት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የሦስቱን ሀገራት መሪዎች በመጥቀስ ድርድሩን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ፕሬዝዳንት ራማፎዛ አድንቀዋል፡፡ ሶስቱ ሀገራት በትብብር ፣ በቀና መንፈስ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመስረት ሁሉንም የሚያግባባ ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ እንደሆኑም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት፡፡
ፕሬዝዳንቱ በየትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት በሕብረቱ መሪነት በግድቡ ዙሪያ የሶስትዮሽ ድርድሩ መቀጠል ለጉዳዩ ሰላማዊ እና የሚያግባባ መፍት ለማምጣት ያላቸውን ጠንካራ ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚያመለክት ነው፡፡
በአፍሪካ ሕብረት የማደራደር ሂደት ላይ ያላቸውን እምነት እና በፓን አፍሪካዊነት መርህ መሰረት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማምጣት ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን እንደሚያሳይም አብራርተዋል፡፡
በድርድሩ ሕብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ለተደራዳሪዎች ያረጋገጡት ራማፎዛ ቴክኒካዊ እና ህጋዊ ጉዳዮችን ጨምሮ ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሀገራቱ እንደሚስማሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
“ያለምንም ጥርጥር የሕዳሴ ግድብ ድርድር በስኬት መጠናቀቅ ቀጣናዊ ትስስርን በማፋጠን በቀጣናው ትብብር እና ዘላቂ ልማትን ያሳድጋል ይህም ጠቀሜታው ለመላው አፍሪካ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ፡፡
ድርድሩ የሚካሔደው በሚኒስትሮች አሊያም በመሪዎች ደረጃ ስለመሆኑ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡
ፕሬዝዳንቱ የሕዳሴ ግድቡን በማስመልከት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር ዙሪያም የሰጡት አስተያየት የለም፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” የውሃ ፍላጎቷን ስለሚገታ “አንድ ነገር ማድረግ አለባት” በሚል ጸብ አጫሪ እና ግብጽን ለጦርነት የሚያበረታታ የሚመስል ንግግር ከእስራኤል እና ከሱዳን መሪዎች ጋር ባለፈው ዓርብ በስልክ ባደረጉት ውይይት ላይ አንስተዋል፡፡ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በውይይቱ ወቅት የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በሚካሔደው ውይይት እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን ንግግር በመቃወም የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ ከማውጣትም ባለፈ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር በመጥራት በንግግሩ ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የተለያዩ የአሜሪካ ሰሴናተሮችን እና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ በበርካታ አካላትም ተተችቷል፡፡