ግብጽ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወደ ሲናይ ማፈናቀል ከእስራኤል ጋር ጦር ያማዝዘኛል አለች
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለማስወጣት የውሃ፣ ነዳጅ እና ኤሌክትሪክ አቅርቦት አቋርጣለች ብለዋል
ግብጽ በራፋህ የድንበር መተላለፊያ ፍልስጤማውያንን እንድታስገባ እየተጠየቀች ነው
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት ተቃውመዋል።
ፕሬዝዳንቱ በካይሮ ከሚገኙት የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ጋር በሰጡት መግለጫ፥ እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከጋዛ በማስወጣት ነጻ ሀገር የመመስረት ትልማቸውን ለማጨለም እየሰራች ነው ብለዋል።
ቴል አቪቭ በጋዛ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ እና ነዳጅ ያቋረጠችው ፍልስጤማውያን ቀያቸውን ለቀው ወደ ሲናይ በርሃ እንዲሰደዱ በማሰብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
“ፍልስጤማውያንን ከዌስትባንክ ወደ ዮርዳኖስ ወይም ከጋዛ ወደ ሲናይ በርሃ ማስገባት አንድ አይነት ነው፤ የአመታት ጥያቄያቸውን ማዳፈን ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት አልሲሲ በመግልጫቸው።
ሚሊየኖችን ከጋዛ ወደ ግብጽ የማስገባቱ እቅድ ግብጽን የጦርነቱ ተሳታፊ ያደርጋታል ያሉት አልሲሲ፥ ፍልስጤማይውያኑን በሲናይ የማስፈር እቅድ ካለ በፍጹም እንደማይቀበሉት አብራርተዋል።
እስራኤል በጦርነቱ ፍልስጤማውያን ንጹሃን እንዳይጎዱ ካሰበች በኔጌቭ በርሃ ታስፍራቸው የሚል ሃሳባቸውንም አክለዋል።
ግብጻውያን ፍልስጤማውያንን ወደ ሲናይ በርሃ የማስፈር እቅድ አጥብቀው እንዲቃወሙም ነው የጠየቁት።
በቴልአቪቭ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግብጽ በራፋህ የድንበር መተላለፊያ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ድንበሯን እንድትከፍት እና የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር በዮርዳኖስ ለመምከር ቀጠሮ ይዘው ነበር።
ትናንት ምሽት በጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃትን ተከትሎ ግን ውይይቱ መሰረዙን የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።