ግብጽ በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያት ከስዊዝ ካናል የምታገኘው ገቢ በ40 በመቶ ቀነሰ
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት የቀይ ባህር ትራንስፖርት ላይ የፈጠረው እክል እንደቀጠለ ነው
ግብጽ ከስዊዝ ካናል በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ታገኝ ነበር
ግብጽ በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያት ከስዊዝ ካናል የምታገኘው ገቢ በ40 በመቶ ቀነሰ፡፡
አራት ወራት ሊሆኑት ጥቂት ቀናት የቀረው የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መቋጫ ያላገኘ ሲሆን የዓለምን ኢኮኖሚ በመጉዳት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጦርነት አሜሪካ ለእስራኤል የቀጥታ ድጋፍ ማሳየቷን ተከትሎ የየመን ሂቲ አማጺያን ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች በመምታት ላይ ናቸው፡፡
ይህንን ተከትሎም የቀይ ባህር ትራንስፖርት በስጋት የተሞላ በማድረጉ የዓለም ሎጅስቲክስ ኩባንያዎች ይህን የንግድ መስመር ከመጠቀም እየተቆጠቡ ይገኛሉ፡፡
የግብጹ ስዊዝ ካናል ዋነኛ የመርከቦች መተላለፊያ ሲሆን በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያት ያስተናግዳቸው የነበሩ ደንበኞቹ መቀነሳቸው ተገልጿል፡፡
አዲሱ የፈረንጆቹ 2024 ከገባ ወዲህ ባሉት ቀናት ያስተናገዳቸው መርከቦች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ቅናሽ ማሳየታቸውን አልአረቢያ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ስዊዝ ካናል የሚያስተናግዳቸው መርከቦች ቁጥር በ30 በመቶ እንደቀነሰ የስዊዝ ካናል ባለስልጣን ሀላፊ ኦሳማ ራቢ ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት በቶሎ እልባት ካልተበጀለት የዓለምን ንግድ የበለጠ ሊጎዳው እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባህር ግዙፍ የጥቃት ሙከራ አደረገ
ስዊዝ ካናል የግብጽ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሲሆን በየዓመቱ የምታገኘው ገቢ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣት ላይ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ግብጽ ከስዊዝ ካናል ባሳለፍነው 2023 ዓመት 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ በ2022 ደግሞ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡
የዓለምን ንግድ በማሳለጥ የሚታወቀው የስዊዝ ካናል በዓመት 25 ሺህ መርከቦች የሚመላለሱበት ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን በላይ እቃም ይጓጓዝበታል፡፡