ግብጽ፤ ኢትዮጵያ ግድቧን በሞላች በማግስቱ፤ የመስኖ ሚኒስትሯን ቀየረች
ካይሮ የህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር ሙሌት በተጠናቀቀ በማግስቱ ነው መሐመድ አብደል አቲን የሻረችው
ሐኒ ሰዊላም መሐመድ አብደል አቲን ተክተው በመስኖ ሚኒስትርነት በፕሬዝዳንት አል ሲሲ ተሾመዋል
የግብፅ የመስኖ ሚኒስትሩ መሐመድ አብደል አቲ ተሽረው በአዲስ ተተክተዋል።
መሐመድ አብደል አቲ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድቧን ለሶስተኛ ጊዜ ሞልታ ባጠናቀቀች በማግስቱ ነው በፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የተሻሩት።
የካቢኔ ሹም ሽር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሲሲ ሐኒ ሰዊላምን በመሐመድ አብደል አቲ ቦታ የመስኖ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል።
ሐኒ ሰዊላም የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮፌሰር ናቸው። በካይሮ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲም ያስተምራሉ።
ግድቡን የተመለከተው የሶስትዮሽ ድርድር ገና መቋጫ አላገኘም። ግንባታው የማገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል የሚል ጥያቄን ደጋግማ የምታነሳው ግብጽ የግድቡን ሙሌትና አስተዳደር የተመለከተ አሳሪ ስምምነት እንዲኖር ያቀረበችው ጥያቄ በኢትዮጵያ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ይህ ባለበት ሁኔታም ነው ኢትዮጵያ ግድቧን ለሶስተኛ ጊዜ ሞልታ ሁለት ተርባይኖቿን ስራ ያስጀመረችው። ይህም መሐመድ አብደል አቲ ለመሻራቸው ምክንያት ሆኗል እንደ ሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘገባ።
ፕሬዝዳንት ሲሲ ሌሎች የካቢኔ ሹም ሽሮችንም አድርገዋል። መስኖን ጨምሮ የ13 ካቢኔ አባላት ሹም ሽርም ነው በፕሬዝዳንቱ የተደረገው።
የጤና፣ የቱሪዝም፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ፣ የሲቪል አቪየሽን፣ የትምህርት እና ሌሎች ሚኒስትሮችንም በአዲስ ተክተዋል።
ሆኖም የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የፋይናነስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አልቀየሩም።
ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባን ያደረገው የሃገሪቱ ፓርላማም በፕሬዝዳንቱ የቀረበውን ሹም ሽር በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።