ኢትዮጵያ ሶስቱ ሀገራት በ2015 የተፈራረሙትን ስምምነት መጣሷንም ሁለቱ ሀገራት ገልጸዋል
ግብፅ እና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ተቃውመዋል።
ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግንባተው መሰረተ የተጣለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዛሬ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጉባ ተገኝተው ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች አንዱ ማለትም ዩኒት 10 በመባልየሚጠራው ተርባይን 375 ሜጋዋት ሀይል የማመንጨት ስራን አስጀምረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀይል ማመንጨት ተከትሎ የግብጽ እና ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥተዋል።
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ እንዳሉት የኢትዮጵያ አካሄድ ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2015 በካርቱም ያደረጉትን የመርህ ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል።
በሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዳሴው ግድብ ተወካይ አምባሳደር ኦማር አልፋሩቅ ለአል ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት፤ ግድቡ ሀይል ማመንጨቱ ሶስቱ ሀገራት የተናጥል እርምጃ እንዳይወስዱ በሚል የፈረሙትን የካርቱም ስምምነትን የሚጥስ እና ወዳጅነታቸውን የሚጎዳ ነው።
ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ “የግድቡ ሀይል ማመንጨት መጀመር ለአህጉራችን እንዲሁም አብረናቸው ሰርተን በጋራ ለመጠቀም ለምንሻ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የምሥራች ነው። ዐባይ ወንዛችንን ሀገራችንን አልምቶ ጎረቤቶቻችንን ሊያረሰርስ ጉዞውን ቀጥሏል” ብለዋል።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ወንድም የሱዳን እና የግብጽ ህዝቦች ዛሬ የተጀመረው ኃይል የማመንጨት ስራ ለእናንተም በረከት ነው እና እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
“ባልተገባ ሁኔታም ቢሆን ለፈጠራችሁት ተጽእኖ እና ፈተናም ለመሰግናችሁ እወዳለሁ፤ መላው የዓለም ህዝብ እንዲገነዘብ የምፈልገው፤ ይህ ውሃ እንደምታዩት ኃይል እያመነጨ ወደ ሱዳን እና ግብጽ የሚሄደ እንጂ፤ ሲነገር እንደነበረው ኢትዮጵያ ውሃውን ገድባ ወንድም የግብጽ እና የሱዳን ህዝብን የማስራብ እና የመስጠማት ፍላጎት እንደሌላት በተግባር ያሳየንበት ነው፤ ለዚህም ደስ ብሎናል ብለዋል።“
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት የመረሰት ድንጋይ ካስቀመጠች አንድ አመት በኋላ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱደን በግድቡ ላይ ስጋት እንዳላቸው ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በግድቡ አስተዳደር ጉዳይ የሶስትዮች ንግግር እና ድርድር ከመጀሩ ቆይተዋል፤ ነገርግን እስካን ከስምምነት አልደረሱም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን እየገነባ ያለው ለልማት አላማ ብቻ መሆኑን እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የጎላ ተጽእኖ እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ግብጽና ሱዳን ግን በግድቡ ዙሪያ የየራሳቸው አቋም አላቸው፡፡
በተለይም ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመ ስምምነትን ጭምር በመጥቀስ፤ ታሪካዊ የሆነ የውሃ ድርሻዋ ላይ ተጽእኖ እንሚያሳድር እና ግድቡ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድርባት ትገልጻለች፡፡
በ2013 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሽንግተን ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ከፈረስ በኋላ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት እንዲካሄድ ተስማምተዋል፡፡
ድርድርሩ ወደ አፍሪካ ህብረት የመጣው ኢትዮጵያ፤ ድርድሩ ሳይጀመር የታዛቢነት ሚና የነበራቸው አሜሪካና የአለም ባንክ ሚናቸውን ወደ አደራዳሪነትና ወደ የስምምነት ሰነድ አርቃቂነት ከፍ በማድረጋቸው እና ኢትዮጵያም ይህን አልቀበልም በማለቷ ነው።
ኢትዮጵያ የግድቡ ጉዳይ የልማት ጉዳይ ነው ብትልም ፤ግብጽና ሱዳን የግድቡን ጉዳይ የጸጥታ ጉዳይ ነው በማለት ለተመድ የጸጥታው ም/ቤት በማቅረብ ም/ቤቱ ወይይት አድርጎበት ያውቃል።