ፖለቲካ
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በህዳሴው ግድብና በኢትዮጵያ ወቅቃዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ተወያዩ
ውይይቱ በሌሎች ጎረቤት ሃገራት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ጭምር ያተኮረ ነበር ተብሏል
በውይይቱ ስለ መጪው የአፍሪካ ህብረት-አሜሪካ ጉባኤም ተነስቷል
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የቀጣናው ሃገራት ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ተወካይ ጋር ተወያይተዋል።
ሐመር ከህብረቱ የፖለቲካ፣ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲዎዬ ጋር ነው የተወያዩት።
በህብረቱ የአሜሪካን ጉዳይ የሚከታተሉት ሚካ ክሌቨርሌይም በህብረቱ ጥላ ስር የኢትዮጵያን መንግስት እና ህወሓትን በማደራደር ለግጭቶች ሰላማዋዊ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚደረጉ ጥረቶችን በተመለከተ በተደረገው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ጎረቤት ሃገራት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ጭምር ያተኮረ ነበር ተብሏል።
ደቡብ ሱዳንን፣ ሱዳንን እና ሶማሊያን በተመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ያስታወቁት ኮሚሽነር ባንኮሌ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይም ላይ አውርተናል ብለዋል።
ኮሚሽነሩ ስለ መጪው የአፍሪካ ህብረት - አሜሪካ ጉባኤ መወያየታቸውንም ነው የገለፁት።
ማይክ ሐመር በአፍሪካ ቀንድ ከከአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ አኒታ ዌበር ጋር በመሆን ትናንት ማክሰኞ፤ ሐምሌ 26 ቀን ወደ መቀሌ አቅንተው ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መምከራቸውን ይታወሳል።