ግብፅ፤ በባለፉት 6 ዓመታት ከ30 ሺ ሜጋ ዋት በላይ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረቷን ገለፀች
ካይሮ ከአጠቃላይ የኃይል ፍጆታዋ 25 በመቶ ያህሉን ሊሸፍን የሚችል ትርፍ የኃይል ምርት እንዳላትም ገልጻለች
ከ2015 ጀምሮ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ራሴን ችያለሁም ነው ያለችው
ግብፅ፤ በባለፉት 6 ዓመታት ከ30 ሺ ሜጋ ዋት በላይ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረቷን ገለፀች።
ምርቱ በኤሌክትሪክ ኃይል ምርት ሙሉ በሙሉ ራስን ከመቻል ባሻገር የተሻለ ትርፍ የኃይል ክምችትን ለመያዝ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ያስቻለ ነው።
ይህ "ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ" የሆነ ነው፤ እንደ ኤሌክትሪክ እና ታዳሽ ኃይል ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ አይማን ሃምዛ ገለጻ።
ቃል አቀባዩ ምርቱ በቅርቡ ከተገነቡ አዳዲስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የተገኘ ነውም ብለዋል።
አዳዲሶቹ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በቡሩለስ፣ በቤኒ ሱፍ እና አዲስ በመገንባት ላይ ባለው አስተዳደራዊ ከተማ (ኒው ካፒታል) የሚገኙ ናቸው። በፈረንጆቹ 2018 ስራ የጀመሩ ሲሆን በድምሩ 14 ሺ 400 ሜጋ ዋት ኃይልን ያመነጫሉ።
ግብፅ ከ2015 ጀምሮ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ራሷን መቻሏን የገለፁት አይማን እስከ 25 በመቶ ሊሸፍን የሚችል ትርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት በብሔራዊ የኃይል ቋታችን አከማችተናልም ብለዋል።
ይህ ለዘመናት በተለይም በእንዲህ ዐይነት የክረምት ወራት ያጋጥም የነበረው የኃይል መቆራረጥ ቆሞ የተሻለ ኃይል ወደማከማቻ ቋት መግባቱን የሚያሳይ ነው እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ።