አመርን ማን ሊተካ እንደሚችል ግን አልታወቀም
የግብጽ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አማካሪ ሆነው ተሾሙ፡፡
ጣሪቅ አመር በራሳቸው በፕሬዝዳንት አል ሲሲ ነው አማካሪ ሆነው የተሾሙት፡፡ጣሪቅ አመር ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ ነው በብሔራዊ ባንክ ገዢነት ሃገራቸውን ያገለገሉት፡፡
በሃገሪቱ ህግ መሰረት አንድ የባንክ ገዢ ለአራት ዓመታት እንዲያገለግል የሚሾም ሲሆን ለሁለት የገዢነት ዘመናት ብቻ ነው የሚያገለግለው፡፡
የመጀመሪያዎቹን አራት ዓመታት በ2019 ያጠናቀቁት አመርም በ2020 ጥር ላይ በድጋሚ ተሾመው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡ ሆኖም አሁን የገዢነት ዘመናቸው መጠናቀቂያ ገና ሳይቃረብ ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው፤ ለፕሬዝዳንት ሲሲ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡
የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት እና ገንዘብ (የግብጽ ፓውንድ) በተዳከመበትና ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዙ ምጣኔ ሃብታዊ ጫናዎች እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት ገዢው ስልጣን መልቀቃቸው እያነጋገረ ነው፡፡
አመር ግን "በፕሬዝዳንት ሲሲ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞዎችን ለሚያስቀጥሉ ለሌሎች አድል ለመስጠት ነው" የሚል ምክንያትን አስቀምጠዋል፡፡
የመልቀቂያ ደብዳቤውን የተቀበሉት ሲሲም አማካሪያቸው አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ ሆኖም ማን ሊተካቸው እንደሚችል አላስታወቁም፡፡
ከሰሞኑ የካቢኔ ሹም ሽር በማድረግ ላይ ያሉት ሲሲ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቧን ለሶስተኛ ጊዜ በሞላች በማግስቱ የውሃ ሃብት እና የመስኖ ሚኒስትሩን መሐመድ አብዱል አቲን በሐኒ ሰዊላም መተካታቸው የሚታወስ ነው፡፡