የግብጽ ፕሬዝዳንት ወደ ቱርክ ሲያቀና ይህ ከ12 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ወደ ቱርክ ለይፋዊ ጉብኝት አቅንተዋል፡፡
ለአስርት አመታት በዲፕሎማሲያዊ ውትረጥ ውስጥ የከረሙት ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ከተስማሙ ወዲህ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን ባሳለፍነው የካቲት ወር ወደ ካይሮ ተጉዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አልሲሲ በአንካራ አየር መንገድ ሲደርሱ ኤርዶሀን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በ2013 አብዱልፈታህ አልሲሲ የሙስሊም ብራዘር ሁድ መሪውን ሞሀመድ ሙርሲን ከስልጣን አንስተው መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ በካይሮ እና በአንካራ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል፡፡
ቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማሻሻል በወሰደችው እርምጃ ከግብጽ ባለፈ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ሳኡዲ አረብያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አድሳለች፡፡
ባሳለፍነው አመት አምባሳደሮችን የተለዋወጡት ሁለቱ ሀገራት አመታዊ የንግድ ግንኙነታቸውን ከ5 ቢሊየን ወደ 15 ቢሊየን ለማሳደግም ተስማምተዋል፡፡
ሶማሊላንድ ግብጽ ወታደሮቿን በሶማሊያ ማሰማራቷን አጥብቃ እንደምትቃወም ገለጸች
በዛሬው እለት ወደ አንካራ ያቀኑት አልሲሲ ከቱርኩ አቻቸው ኤርዶሀን ጋር በሚኖራቸው ውይይት ቀጠናዊ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
የጋዛው ጦርነት እና የተኩስ አቁም ድርድር ሂደደቶች መሪዎቹ ከሚመክሩባቸው ቀጠናዊ አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀገራቱ ትብብራቸውን በሚያጠናክሩ የተለያዩ ትብብሮች ላይ እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡
መከላከያ ፣ ኢነርጂ ፣ ቱሪዝም ፣ ጤና ፣ ትምህርት እና ባህልን ጨምሮ 20 የትብብር ማዕቀፎች ፊርማቸውን የሚያኖሩባቸው ሰነዶች ናቸው፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ስለሚያንጸባርቋቸው ሀሳቦች የጋራ መግለጫ የሚያወጡ ሲሆን በተጨማሪም የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ከሰአታት በኋላ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግለጫ እንደሚሰጡ አስታውቋል፡፡