ባለፈው ሳምንት በእስራኤል መርከብ ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ኢራን መፈጸሟን ጠ/ሚ ኔታንያሁ ገለጹ
የኢራንን ጥቃት ለመከላከል እስራኤል ማንኛውንም እርምጃ እንደምትወስድ ጠ/ሚኒስትሩ ገልጸዋል
ኢራን በእስራኤል የቀረበባትን ክስ አልተቀበለችም
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት በኦማን ባህረ ሰላጤ በነበረ የእስራኤል መርከብ ላይ ለተፈጠረው ፍንዳታ ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ይሁን እንጂ ቴህራን ክሱን አልተቀበለችውም፡፡
ኤም ቪ ሄሊዮስ ሬይ ተባለው የተሽከርካሪ ጫኝ መርከብ ሐሙስ ማታ እና አርብ ጠዋት መካከል ባለው ጊዜ በተከሰተበት ፍንዳታ በሁለቱም ጎኖቹ መጎዳቱ ተገልጿል፡፡
“ይህ በእርግጠኝነት የኢራን ስራ መሆኑ ግልፅ ነው”ሲሉ ኔታንያሁ ለካን ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል አፀፋዊ ምላሽ ትሰጣለች ወይ ተብለው ሲጠየቁ “ፖሊሲዬን ታውቃላችሁ፡፡ ኢራን የእስራኤል ትልቋ ጠላት ናት፡፡ እሷን ለመከላከል ቆርጯለሁ፡፡ በሁሉም የቀጣናው ክፍል በኢራን ላይ ጥቃት እየፈጸምን ነው” ብለዋል፡፡
ኢራን በመርከቡ ጥቃት ላይ እጇ እንደሌለ ገልጻለች፡፡ የቴህራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሰዒድ ካቲብዛዴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህንን ክስ በጥብቅ እንቃወማለን” ብለዋል፡፡ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ደህንነት ለኢራን እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እስራኤል በሶሪያ በሚገኙ በኢራን የሚደገፉ ኃይሎች እና የኢራን ስምርቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ስትፈጽም የቆየች ሲሆን ትናንት ምሽትም በደቡብ ደማስቆ እስራኤል የሚሳይል ጥቃት መፈጸሟን ሶሪያ አስታውቃለች፡፡
ኢራን በእስራኤል ተገድሎብኛል ላለችው ከፍተኛ የኑክሌር ሳይንቲስት ግድያ “የተሰላ” ምላሽ እንደምትሰጥ ህዳር ወር ላይ መግለጿ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ክስ እስራኤል የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡