ግብጽ በአዲሱ የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ እንደምትሳተፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አረጋገጡ
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ከተስማሙ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ ስለመቀጠሉ ይፋዊ መረጃዎች አልወጡም
በትላንትናው እለት በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ ወደ አዲስአበባ ማቅናቱ ተገልጿል
ግብጽ አትሚስን በሚተካው በአዲሱ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) ውስጥ እንደምትሳተፍ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል በሶማሊላንድ የወደብ የመግባብያ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በተፈጠረው የዲፕሎማሲ ውጥረት የካይሮ እና የሞቃዲሾ ግንኙነት መጠናከሩ ይታወሳል፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዳላቲ ካይሮ ከሶማሊያ መንግስት በቀረበላት ጥያቄ መሰረት በአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ትሳተፋለች ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን በሁሉም የሶማሊያ ብሔራዊ መሬት ላይ እንድታስከብር ፣ አንድነት እና ደህንነቷን የሚነኩ መመሪያዎችን ወይም የአንድ ወገን እርምጃዎችን ለመቃወም የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን” ብለዋል፡፡
በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤታሞች መካከል ልዩነት መፈጠሩን ተከትሎ ወደ ቀጠናው ለመቅረብ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች የምትገኝው ግብጽ በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ሀይል 5 ሺህ ፣ ከሶማሊያ ጋር በሚደረግ የሁለትዮሽ ስምምነት ደግሞ ተጨማሪ አምስት ሺ ወታደሮችን የማስፈር ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ግብጽ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ) የሰራ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈች እንደምትገኝ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ካይሮ የሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎች ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታጣቂዎች ለመዋጋት በሚያደርጉት ጥረት ስልጠና እና ድጋፍ እየሰጠች እንደምተግኝ ዘ ናሽናል አስነብቧል፡፡
የጦር መሳሪያዎችን፣ወታደራዊ አማካሪዎችን፣ አሰልጣኞችን እና የፀረ ሽብር ኮማንዶዎችን አስቀድማ ወደ ሞቃዲሾ ልካለች።
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (አውሶም) በ2024 መጠናቀቂያ ከቀናት በኋላት አትሚስን በመተካት የሚሰማራ ይሆናል፡፡
በቱርክ አደራዳሪነት ከአመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአንካራ ፊት ለፊት የተገናኙት የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መሪዎች በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባብያ ስምምነት ካልተሰረዘ በአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የኢትዮጵያ ጦር እንዲሳተፍ አልፈቅድም የሚል አቋም ስታንጸባርቅ የቆየችው ሶማሊያ በዚህ ዙሪያ ሀሳቧን ስለመቀየሯ ወይም የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ ስለመቀጠሉ ይፋዊ መረጃዎች አልወጡም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊያ የውጭጉዳይ ሚኒስትር ትላንት ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኦማር የተመራ ልዑክ ወደ አዲስአበባ እንደሚያቀና አስታውቋል፡፡
ይህ የሶማሊያ መንግስት ልዑክ ሞቃዲሾ ከአዲስአበባ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኛነት ያሳያል ብሏል መግለጫው፡፡