ግብጽ ገንዘቧን ካዳከመች ከሰአታት በኋላ ከአይኤምኤፍ ብድር አገኘች
በአሁኑ ወቅት የግብጽ ፓውንድ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞ አንድ ዶላር በ50 የግብጽ ፖውንድ እየተመነዘረ ይገኛል
ባንኩ ፓውንድ በነጻ ገበያ እንዲመነዘር የወሰነው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ኢንቨስትመንት ለመጨመር እና የአይኤምኤፍን ፍላጎትን ለማሟላት ነው ተብሏል
ግብጽ የመገበያያ ገንዘቧን ካዳከመች ከሰአታት በኋላ ከአይኤምኤፍ ብድር አገኘች።
የግብጽ ብሔራዊ ባንክ የግብጽ ፖውንድ የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጉን ካሳወቀ ከሰአታት በኋላ ከአለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የ8 ቢሊዮን ዶላር ብድር አግኝታለች።
ከዚህ በተጨማሪም ግብጽ ለዘላቂ ልማት ስራዎች የሚውል 1.2 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚሰጣት ሲሆን ይህ ሀገሪቱ ከአይኤምኤፍ ያገኘችውን አጠቃላይ ብድር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚያደርገው ሮይተርስ ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅት የግብጽ ፓውንድ በከፍተኛ ደረጃ የተዳከመ ሲሆን አንድ ዶላር በ50 የግብጽ ፓውንድ እየተመነዘረ ይገኛል።
ይህ አሀዝ ግብጽ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ከ30.85 የግብጽ ፓውንድ እንዳይበልጥ ለወራት አስቀምጣው ከነበረው ገደብ በእጅጉ የሚበልጥ ነው።
ባንኩ ፓውንድ በነጻ ገበያ እንዲመነዘር የወሰነው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ኢንቨስትመንት ለመጨመር እና የአይኤምኤፍን ፍላጎትን ለማሟላት ነው ተብሏል።
ግብጽ ቀደም ሲል የገንዘብ ምንዛሬ በገበያ እንዲተመን እንደምታደርግ እና ፖውንድ የሚዳከም ከሆነ ግን ወደመቆጣጠር እንደምትመለስ ስትገልጽ ነበር።
በዚህ ወቅት ግን ግብጽ ከአረብ ኢምሬትስ ጋር የካቲት ወር መጨረሻ የተፈራረመችውን የ35 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጨምሮ ወደ ሀገር ውሰጥ በሚገባው የውጭ ምንዛሬ ፖውንድን ጨርሶ ከመውደቅ ይታደገዋል ብላ ተማምናለች።
ብሔራዋ ባንኩ ውሳኔውን ይፋ ካደረገ በኋላ የግብጽ አለምአቀፍ ቦንዶች ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን የረጅም ጊዜ ቦንዶች ትልቅ ትርፍ ያገኛሉ ተብሏል።
ባለፈው አመት ሪከርድ የሰበረውን እና በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለችግር የዳረገውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በማሰብ ባንኩ የማበደሪያ ወለድን ወደ 28.25 በመቶ እንዲሁም የማስቀመጫ ወለድን ደግሞ ወደ 27.25 በመቶ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍ አድርጎታል።
የብሔራዊ ባንኩ ገዥ ሀሰን አብደላህ በገንዘቡ ምንዛሬው ላይ ትክክለኛ ያልሆኑ አካሄዶች ከተከሰቱ ባንኩ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ተናግረዋል።