ጦርነት ባይቆምም ሩሲያ እና ዩክሬን ድርድር ላይ ናቸው
የሩሲያ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ ለመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲውል ጥያቄ ማቅረቧን ዩክሬን አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የአኮኖሚ አማካሪ ኦሌግ ኡስቴንኮ እንዳሉት በተለያዩ ሀገራት ባንኮች ያለው የሩሲያ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ ሊውል ይገባል ሲሉ ለሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል፡፡ ሩሲያ 400 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ የታገደባት ሲሆን ይህ እንዲሰጣትም ነው ዩክሬን የጠየቀችው፡፡
መጀመሪያ መነጋገር የሚገባው በሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ በነበረውና በታገደው 300 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ላይ እንደሆነም የቮሎድሚር ዘለንስኪ አማካሪ ተናግረዋል፡፡ ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት እስከ 500 ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ይህንንም ከምዕራባውያን ጭምር ለማግኘት ታቅዷል ተብሏል፡፡
ብዙ ፖለቲከኞች በሩሲያ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆሙ አላስቻላቸውም እያሉ ነው፡፡
የዩክሬን ፖለቲከኞች አሁን ላይ ጦርነቱ በይፋ ባይቆምም ሀገሪቱን መልሶ ስለመገንባት ግን አስተያየቶችን እየሰጡ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ሩሲያ እና ዩክሬን ድርድሮችን እያደረጉ ቢሆንም ጦርነቱ ላይ ግን የተለወጠ ነገር እንደሌለ ተገልጿል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችባትና “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ብላ በሰየመችው ጦርነት ምክንያት በዚህ ሩብ አመት ኢኮኖሚዋ 16 በመቶ ቀንሷል፡፡ በፈረንጆቹ 2022 ደግሞ በጥቅሉ ኢኮኖሚዋ በ40 በመቶ እንደሚቀንስ ይፋ ሆኗል፡፡