የግብጽ አዲሱ የደህንነት ሃላፊ ማህሙድ ረሻድ ማን ናቸው?
በግብጽ የስለላ ተቋም ለረጅም አመታት ያገለገሉት ማህሙድ ረሻድ ከ2018 ጀምሮ ተቋሙን ሲመሩ የነበሩትን አባስ ከማል ተክተዋል
የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ አባስ ከማል ደግሞ የፕሬዝዳንት አልሲሲ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በትናንትናው እለት ሜጀር ጄነራል ሀሰን ማህሙድ ረሽዳን የሀገሪቱ የደህንነት ተቋም (ጂአይኤ) ሃላፊ አድርገው ሾመዋል።
አዲሱ የደህንነት ሃላፊ ከ2018 ጀምሮ ተቋሙን ሲመሩ የነበሩትን ሜጀር ጀነራል አባስ ከማል ተክተዋል።
ማህሙድ ረሽዳ በፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ፊት ቀርበው ቃለመሃላ በመፈጸም ስራቸውን በይፋ መጀመራቸው ተዘግቧል።
የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ ሜጀር ጀነራል አባስ ከማል ደግሞ የፕሬዝዳንት አልሲሲ ልዩ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አባስ ከማል ከደህንነት ተቋሙ መሪነት የተነሱበትን ምክንያት አልጠቀሰም።
አዲሱ የግብጽ የደህንነት ተቋም ሃላፊ ማን ናቸው?
ሀሰን ማህሙድ ረሻድ ከካይሮ ወታደራዊ ቴክኒክ ኮሌጅ በወታደራዊ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በግብጽ የደህንነት አገልግሎት ለረጅም አመታት ያገለገሉት ረሻድ የተለያዩ የሃላፊነት እርከኖችን አልፈው የአባስ ከማል ምክትል ሆነው እስከማገልገል ደርሰዋል።
አዲሱ ሹም ሜጀር ጀነራል ከመሆናቸውና በስለላ ተቋሙ ለረጅም ጊዜ ማገልገላቸው ከመገለጹ ውጭ ማንነታቸውን በዝርዝር የሚጠቅስ መረጃ አልወጣም።
የግብጽን የሀገር ውስጥ እና የውጭ የደህንነት ጉዳዮች የሚከታተለው ተቋም በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የተካሄዱ ድርድሮች ላይ ጉልህ ድርሻ ነበረው።
በሱዳን እና ሊቢያ በሚካሄዱ ጦርነቶች የካይሮን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማስፈጸምም የደህንነት ተቋሙ ትልቅ ሚና መጫወቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
አዲሱ የደህንነት ሹም ማህሙድ ረሻድ የቀድሞ አለቃቸው የጀመሩትን የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር የማስቀጠል ተግባር ቀዳሚ ስራቸው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።