ግብፅ፣በናይል ላይ ጥገኛ የሆነውን ህዝብ የሚጎዳ የአንድ ወገን ውሳኔን እንደማትቀበል ገለጸች
አልሲሲ እና ካጋሜ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያይተዋል ተብሏል
የሩዋንዳ እና ግብፅ ሀገራት መሪዎች በአምስት ዘርፎች ላይ በጋራ እንሰራለን ብለዋል
የግብፁ ፕሬዝዳንት ሀገራቸው በናይል ወንዝ ላይ ጥገኛ የሆነን ሕዝብ የሚጎዳ የአንድ ወገን ውሳኔን እንደማትቀበል ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ካይሮን እየጎበኙ ላሉት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መሆኑን የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ፖል ካጋሜ በበኩላቸው በግብፅ መዲና ካይሮ ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸውን በይፋዊ የማህበራዊ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አልሲሲ የናይል ወንዝ ብቸኛ የህይወትና የልማት ምንጭ በመሆኑ የትኛውም የተፋሰስ ሀገር ብቻውን መወሰን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ አብዱል ፋታህ አልሲሲ ከሩዋንዳው አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት “የአንድ ወገን ውሳኔን አንቀበልም” ከማለት የዘለለ የሀገራትን ስም አለመጥቀሳቸው ተገልጿል፡፡
አልሲሲ ምንም እንኳን የሀገራትን ስም ባይጠቅሱም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አዳዲስ ጉዳዮች ዙሪያ ከፖል ካጋሜ ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብር እንዲኖር እንደሚፈልጉም አልሲሲ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ከግብፅ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸውን የተገለጸ ቢሆንም በናይል ወንዝም ሆነ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት መኖር አለመኖሩ አልተገለጸም፡፡ ግብፅ እና ሩዋንዳ በተለያዩ መስኮች ላይ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ማድረጋቸውን ፖል ካጋሜ አስታውቀዋል፡፡
ኪጋሊ እና ካይሮ፤ በዲፕሎማቶች ስልጠና፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በሙዚየም፣ በወጣቶችና በስፖርት ዙሪያ ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨቱን ካስታወቀች በኋላ፤ የግብፅ እና የሩዋንዳ ፕሬዝዳንቶች በአካል ሲገናኙ የዛሬው የመጀመሪያ ነው፡፡
aXA6IDE4LjIxOS4yMzYuMTk5IA== ejasoft island