የግብፅ እና የአረብ ኤምሬትስ መሪዎች የሁለትዮሽ ውይይትም አድርገው ነበር
የአረብ ኤምሬትስ፣ የእስራኤልና የግብፅ መሪዎች በግብፅ የሦስትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ውይይት ያደረጉት የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን፤ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔትና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ናቸው።
መሪዎቹ፤ የሦስትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸው ተሰምቷል።
የሶስቱ ሀገራት መሪዎች፤ በአቡዳቢ፣ በቴላቪቭ እና በካይሮ መካከል በሚኖረው ትብብር፣ ትስስርና ምክክር ላይ ያተኮረ ውይይትም አድርገዋል ነው የተባለው።
ይህ ትብብር፣ ትስስርና ምክክር በቀጣናው ሰላምና ልማትን እንዲሁም የኃይል አቅርቦትን ዓለም አቀፍ የገበያ መረጋጋትን ለማምጣት እንደሚግዝ ተገልጿል።
የሀገራቱ መሪዎች በዝርዝር ባልተገለጹ እና ቁጥራቸው በርከት ባሉ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪም ውይይት ማድረጋው ነው የተገለጸው።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ፤ ወቅታዊ በሆኑ ቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በመሪዎቹ መካከል የሃሳብ መለዋወጥ እንደነበር አንስተዋል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንዳለው በኃይል አቅርቦት፣ በገበያ መረጋጋት፣ በምግብ እጥረትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል ብሏል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ትናንትና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተቀብለው የነበረ ሲሆን፤ የሁለቱ ሀገራት ልዑካን በተገኙበት የሁለትዮሽ ንግግር አድርገው ነበር ተብሏል።
ልክ እንደ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ሁሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ግብፅ የገቡት ትናንትና እንደነበር ተገልጿል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሁኑን ጨምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ግብፅን ለሁለተኛ ጊዜ ጎብኝተዋል።