የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የስንዴ ፈላጊዎችን አስግቷል እየተባለ ነው
ሕንድ ግብፅን ጨምሮ ለሌሎች ሀገራት ስንዴ ልትሸጥ መሆኑን የሀገሪቱ ንግድ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
ኒውዴልሂ ለካይሮ ስንዴ ለመሸጥ ማቀዷን የገለጸች ሲሆን የማጓጓዝ ስራውም እንደሚጀመር ተገለጿል።
አሁን ላይ በዋናነት ስንዴን በመሸጥ የሚታወቁት ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ሕንድ ዕድሉን ተጠቅማ ሽያጭ እንደምትጀምር ብሉምበርግ ዘግቧል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ መሆናቸው ስንዴን የሚገዙ ሀገራትን ጭንቀት ላይ ጥሏል እየተባለ ነው።
ሕንድ ስንዴ ለመሸጥ ከግብፅ ባለፈም ከቻይና እና ከቱርክ ጋር ንግግር ማድረግ መጀመሯም ተጠቅሷል። የሀገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር፤ የሕንድ መንግስት ለቦሲኒያ፣ ለናይጄሪያ እና ለኢራን ስንዴ ለመሸጥ ንግግር እያደረገ ነው ተብሏል።
ስንዴን በማምረት በዓለም ሁለተኛ የሆነችው ሕንድ እ.አ.አ በ2020/ 2021 ከፍተኛውን የስንዴ ምርት ለባንግላዲሽ መሸጧ ተገልጿል።
የሕንድ መንግስት በቂ ስንዴን ለማጓጓዝ የሚያስችል አስፈላጊ የባቡር መስመር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። የወደብ ባለስልጣናት በበኩላቸው የኮንቴይነር እና የተርሚናል ቁጥር እንዲጨምር ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል።
በሕንድ የንግድ ሚኒስቴር የግብርናና የምግብ ውጤቶች ክፍል ስንዴውን እንደት ማጓጓዝ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጉም ተሰምቷል።
ባንግላዲሽ፣ ኔፓል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፣ስሪላንካ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ኳታር፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኦማንና ማሌዥያ ከሕንድ ስንዴ የሚገዙ ሀገራት ናቸው።