ሀገሪቱ የማሊ ተልዕኮዋን ያቋረጠችው ወታደሮቿ ስለተገደሉባት ነው
ግብጽ በማሊ እያካሄደች ያለውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አቋረጠች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ እየሰፋ የመጣውን የጽንፈኞች ጥቃት ለማስቆም በሚል ግብጽን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ጦር አሰማርቷል።
የዚህ ሰላም ማስከበር አካል የሆነችው ግብጽ በማሊ የተሰማራው ጦሯ ተልዕኮውን እንዲያቆም ማድረጓን ሮይተርስ ዘግቧል።
የግብጽ ጦር ከአንድ ወር በፊት በማሊ መዲና ባማኮ በስራ ላይ እያሉ በተፈጸመባቸው ጥቃት ሁለት ወታደሮቿ የተገደሉ ሲሆን ሀገሪቱ ክስትቱን ተከትሎ ጦሯ ማሊን ለቆ ወደ ካይሮ እንዲመለስ አስገድዶታል።
ባለፉት ዓመታት ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት የተፈጸመባት ማሊ በተመድ ስር ከበርካታ ሀገራት የተውጣጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላም አስከባሪ ጦር ቢሰፍርም የጽንፈኞች ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በስልጣን ላይ ያለው የማሊ ወታደራዊ መንግስት ለነዚህ ሰላም አስከባሪዎች መልካም አመለካከት የለውም በሚል ትችቶች እየቀረቡበት ይገኛል።
በኮለኔል አስሚ ጎይታ የሚመራው የማሊ ወታደራዊ መንግስትም በሰላም ማስከበር ስም የማሊን ሉዓላዊነት እየጣሱ መሆኑን ይናገራል።
ይህ ወታደራዊ መንግስት ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚል በማሊ የሰፈረው የፈረንሳይ ጦር ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ ያደረገ ሲሆን ፈረንሳይም በዚህ ውሳኔ መበሳጨቷን በተደጋጋሚ ተናግራለች።
ማሊ ከአንድ ሳምንት በፊት 49 የኮቲዲቯር ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ለመፈጸም ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ማዋሏ ይታወሳል።
የኮቲዲቯር መንግስት በበኩሉ የታሰሩት 49 ወታደሮች በተመድ ስር ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ማሊ ያቀኑ በመሆኑ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቃለች።