ሃማስ፥ እስራኤል “የፍልስጤሙን ማንዴላ” ከእስር እንድትለቅ ጠየቀ
የፍልስጤሙ ቡድን በእስራኤል ለ22 አመታት በእስር ላይ የሚገኘው ማርዋን ባርጉቲ ይለቀቅ የሚለውን ሃሳብ የተኩስ አቁም ድርድሩ አካል አድርጎታል ተብሏል
ባርጉቲ ፍልስጤማውያን ሀገር ሲመሰርቱ ፕሬዝዳንት ይሆናል ብለው የሚያምኑበት ግለሰብ ነው
እስራኤል በእስር ላይ የሚገኘውን ማርዋን ባርጉቲ እንድትፈታ ሃማስ ጠየቀ።
ሃማስ “የፍልስጤሙ ማንዴላ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ባርጉቲ እንዲለቀቅ በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት እየተካሄደ በሚገኘው የተኩስ አቁም ድርድር መጠየቁን የሃማስ ከፍተኛ አመራር ኦሳማ ሀምዳን ተናግረዋል።
ሃማስ የ64 አመቱ ማርዋን ባርጉቲ እንዲለቀቅ መጠየቁ ፍልስጤማውያንን አንድ የሚያደርግ ቡድን መሆኑን ለማረጋገጥ ያለመ ስለመሆኑ ተነግሯል።
እስራኤል ግን ለሁለት አስርት አመታት በእስር ላይ የሚገኘውን ባርጉቲ ትለቃለች ተብሎ አይጠበቅም።
በፈረንጆቹ 2011 የአሁኑንበጋዛ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋርን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እስረኞች ሲለቀቁ ባርጉቲን አልፈታም ማለቷን ነው አሶሼትድ ፕረስ ያስታወሰው።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት ከ9 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ማሰሯን የእስራኤሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን ሃሞኬድ አስታውቋል።
ሃማስ አራት ወራት ሊደፍን የተቃረበው ጦርነት እንዲቆም እነዚህ እስረኞች ሙሉ እንዲለቀቁ መጠየቁም ነው የተሰማው።
ለአንድ ሳምንት በቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ከ100 በላይ ታጋቾችን ያስለቀቀችው እስራኤል ቀሪ ከ130 በላይ ዜጎቿን ለመታደግ ባርጉቲን ትፈታለች ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
“የፍልስጤሙ ማንዴላ” ማርዋን ባርጉቲ ማን ነው?
ባርጉቲ በፈረንጆቹ 2002 በእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኝ ፍልስጤማዊ ነው።
የፋታህ የወታደራዊ ክንፍ መሪ የነበረው ማርዋን ባርጉቲ በበርካታ የግድያ ወንጀሎች እና የሽብርተኛ ቡድን አባል ሆነሃል በሚሉ ክሶች ዘብጥያ ከወረደ 22 አመታት ተቆጥረዋል።
የፍልስጤም እና እስራኤል ግጭት በተነሳ ቁጥር ስሙ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው ባርጉቲ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖችን ለማቀራረብ በብዙው የደከመ ግለሰብ ነው።
ባርጉቲ ተቀናቃኝ ሃይሎችን የማደራደር ብቃቱና የሰላም ቀናኢነቱን የሚጠቅሱ አካላትም የኖቬል ሽልማት እጩ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥረት ማድረጋቸውን ፍራንስ 24 ያወሳል።
ያሲር አራፋትን የተኩት የ88 አመቱ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ ምርጫ እንዲደረግ አለመፍቀዳቸው እንጂ ባርጉቲ በፍልስጤማውያን ዘንድ ቀዳሚው ተመራጭ እንደሚሆን ይገመታል።
የሃማስ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከእስር ከተለቀቀም የወደፊቷ ነጻ ሀገር ፍልስጤም ፕሬዝዳንት እንደሚሆን የበርካቶች እምነት ነው።