ግብፅ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ሌሎች አማራጮችን እንደምትጠቀም አስታወቀች
የኢፌዴሪ የዉሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ግብጽ ከድርጊቷ እንድትቆጠብ አሳስቧል
በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ም/ቤት መውሰዷን እንደምትቀጥል ሀገሪቱ አስታውቃለች
ግብፅ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ሌሎች አማራጮችን እንደምትጠቀም አስታወቀች
የግብፅ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ እንዳሉት ሀገሪቱ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሌሎች አማራጮችን ለመፈልግ መገደዷን አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት መውሰድ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ የገለጹት፡፡
ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት “በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ የግብጽ ዲፕሎማሲ” በሚል ርዕስ ዛሬ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በታካሔደ አውደ ጥናት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው አል ዐይን አረብኛ እንደዘገበው፡፡
የግብፅ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሕመድ ሀፌዝ በሰጡት መግለጫ ፣ ሀገሪቱ ላለፉት ዓመታት ድርድሩን ለመቀጠል ቁርጠኛ አቋም እንደነበራትና የሶስቱንም ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ፍትሃዊና ትክክለኛ ስምምነት ላይ ለመድረስ ልባዊ ፍላጎት እንዳላትም ሚኒስትሩ በአውደ ጥናቱ ላይ ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ “ግትር አቋም” ባለመቀየሩ ምክንያት የቅርብ ጊዜ ድርድሮች ፍሬያማ እንዳልሆኑም ሚኒስትሩ መናገራቸውን መግለጫው ያትታል፡፡
በመሆኑም ግብፅ ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ም/ቤት መውሰድን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን ለመውሰድ መገደዷን ሳሚ ሽኩሪ ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በግብፅ የውሃ መብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የተናጥል እርምጃዎችን እንዳትወስድ በመከላከል የጸጥታው ም/ቤት ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ የመከላከል ኃላፊነት አለበት” ሲሉ ሚኒስትሩ መናገራቸውንም ነው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ያብራሩት፡፡
ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማደናገር እና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሰደር የሚደረግ ማንኛውም ዘመቻ ወይም ኢትዮጵያ ያልተካተተችበትን በቅኝ ግዛት ላይ የተመሰረቱ ስምምነቶችን እንድትቀበል በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም ሲል የኢፌዴሪ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫ ግብጽ ድርድሩን ለማደናቀፍ የምታደርጋቸውን ጥረቶች እና ኢትዮጵያን የመወንጀል ተግባር እንድታቆም ማሳሰቡ ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ. ሰኔ 13 ቀን 2020 የግብጽ የውሃ ሀብትና የመስኖ ልማት ቃል አቀባይ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳዘነውም ሚኒስቴሩ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡ ቃል አቀባዩ በመግለጫው “ድርድሩ በኢትዮጵያ ምክንያት እየተበላሸ ነው” የሚል ክስ ቢሰነዘርም ፣ እውነታው ግን በድርድሩ ለውጥ እያመጣን መሆኑ ሲሆን በቀጣይ ድርድሩ መሰናክል ቢገጥመው እንኳን ግብፅ በቅኝ ግዛት ላይ የተመሠረተ የውሃ ስምምነትን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ነው ሲልም ሚኒስቴሩ በመግለጫው ይፋ አድርጓ ፡፡ የቅኝ ግዛቱ ስምምነት የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ እና ህጋዊ መብቶቻቸውን የሚደፈጥጥ እንደሆነም ሚኒስቴሩ አስታውሷል፡፡
በእስካሁኑ ድርድር የተገኙ ለውጦችን በመገምገም ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በግብጽ ሊቀመንበርነት ድርድሩ ዛሬ እንደሚቀጥል ይታወቃል፡፡ በዚሁ እለት ታዲያ የግብፅ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ክስ አቅርቧል፡፡
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛለች፡፡
ከግድቡ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ዉጥረት እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድርድሩ እንዲቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው ዉይይት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው ድርድሩ በድጋሚ መካሔድ የጀመረው፡፡