ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ጉዳይ ላይ እጇን እንደማታስገባ ገለጸች
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ላበረከተችው የኮቪድ-19 ድጋፍ አምባሳደሩ ምስጋና አቀረቡ
የህዳሴ ግድብ ለቀጣናው ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ግድቡን እንደምትደግፍ ደቡብ ሱዳን አስታውቃለች
ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ ላይ እጇን እንደማታስገባ አስታውቃለች
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ሞርጋን ሀገራቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ ላይ እጇን እንደማታስገባ አስታወቁ፡፡ ዲፕሎማቱ ይህንን ያሉት ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ዛሬ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቀውና “ደቡብ ሱዳን በግዛቷ ለግብጽ መንግስት የወታደራዊ ካምፕ ግንባታ የሚያገለግል ቦታ ለመስጠት ከግብጽ ጋር ተስማምታለች” በሚል የተናፈሰው ዜና መሰረተ ቢስ መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋጠዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የደቡብ ሱዳን መንግስት መግለጫ ማውጣቱንና ጁባ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል። ደቡብ ሱዳን እንደ ሀገር ራሷን አንድትችል እና የበለጸገች እንዲሁም የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ያረጋገጠች ሀገር እንድትሆን የኢትዮጵያ ድጋፍ የጎላ መሆኑንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ህዝቦች በሁለት ሀገር ውስጥ የሚኖሩ እና በርካታ ነገሮችን የሚጋሩ አንድ ህዝቦች ናቸው ያሉት አምባሳደሩ ፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በመጠቀም የመልማት መብቷን ደቡብ ሱዳን በጽኑ ትደግፋለች፤ ፍላጎቷንም ታከብራለች ብለዋል፡፡
ሁለቱን ሀገራት በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋጋጥ በትብብር እየሰሩ ባለቡት ወቅት የተለየ ተልዕኮ ያላቸው አካለት የሚያደርጉትን ያልተገባ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ለመመከት ትስራለችም ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጄክት በቀጣናው የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት ጉልህ ሚና የሚጫወት እና ለደቡብ ሱዳንም ተነሳሽነትን የሚፈጥር ፕሮጀክት ስለሆነ በደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግስት በኩልም ሙሉ ድጋፍ ያለው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸው ልዩነት የሁሉንም ሀገራት ጥቅም ባማከለና የህዝቦቹን ፍላጎት ባጣጣመ መልኩ በውይይት መፈታት እንዳለበት ደቡብ ሱደን በጽኑ ታመናለችም ብለዋል አምባሳደር ጀምስ ከሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት።
አምባሳደር ጀምስ ኢትዮጵያ በትናንትናው እለት ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ላደረገቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፋም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኢትጵያ ከጉድለቷ የደቡብ ሱዳንን ህዝብ ለመርዳት ላሳየችው ቁርጠኝነት የደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግስት ምስጋናውን ያቀርባልም ብለዋል። አምባሳደር ጄምስ በደቡብ ሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተም ለአቶ ገዱ ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወዳቿን በውል ትረዳለች ስለሆነም ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀውን ዜና ትክክል ነው ብላ እንዳልወሰደችው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ዋጋ ትሰጣለችም ብለዋል ሚኒስትሩ ።