በሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የተለያዩ መግባባቶች ተደረሱ
በድርድሩ የተቀዛቀዘ ተሳትፎ ነበራት የተባለችው ግብፅ ከዚህ ቀደም የደገፈችውን የሱዳንን ሰነድ ተቃውማለች
የመጀመሪያ ዙር የግድቡን የውሃ አሞላል እና መመሪያ በተመለከተ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ
የመጀመሪያ ዙር የግድቡን የውሃ አሞላል እና መመሪያ በተመለከተ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ
በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚካሔደው ድርድር ትናንት ለአራተኛ ቀን ቀጥሎ ውሏል።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ላከልኝ ባወጣውመግለጫ ፣ በሱዳን ሊቀመንበርነት በተካሄደው ድርድር በግድቡ የመጀመሪያ የዉሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ነው ድርድሩ የተካሔደው፡፡
ኢትዮጵያ በድርድሩ ሁለት የቴክኒክና የህግ ቡድኖች ቢኖሩ በሚል ያቀረበችውን ሀሳብ ሱዳን መቀበሏን ሚኒስቴሩ ላከልኝ ባለው መግለጫ ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።
በግብፅ በኩል ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሳትቀበለው የቀረችውን ረዘም ያለ የድርቅ ጊዜን እና ደረቃማ ዓመትን በተመለከተ ዝርዝር ህግ መኖር አለበት የሚለውን ሃሳቧን በድጋሚ አንስታለች።
በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደ ድርድር ፣ የመጀመሪያው ዙር የግድቡን የውሃ አሞላል እና አሞላሉ የሚገዛበት መመሪያን በተመለከተ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሃሳብ ለመቀጠል ከመግባባት መደረሱን ነው ያመለከተው።
ረዥም ድርቅን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴ የውሃ አለቃቁ ላይ ህግን እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት እንዲሰጠው እና ዝርዝር አለቃቀቅን በተመለከተ ግን ድርድር እንደሚያስፈልግ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
እንደዚሁም የግድቡን ደህንነት የተመለከተ ህግ እና ግድቡ በሚኖረው አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ጥናት ማስፈለግ ላይ ተግባብተናልም ነው ያለው መግለጫው።
በዛሬው ዕለት ሦስቱ ሀገራት የድርድር ውጤቶችን የሚያካትቱ መመሪያዎችን እና ደንቦችን ይለዋወጣሉ፡፡
የግብፅ ተደራዳሪዎች በእለቱ የነበራቸው ተሳትፎ የተቀዛቀዘ ነበር ያለው መግለጫው፣ ከተራዘመ የድርቅ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ፍላጎት በማሳወቁ ላይ ብቻ መሳተፋቸውን አመልክቷል።
ሆኖም በመጨረሻ ሰዓት የግብፅ ተደራዳሪዎች ውይይት ሲደረግበት በነበረው እና ከዚህ በፊት ራሳቸው ሊያሰራ የሚችል ሰነድ ነው ብለው አስተያየት የሰጡበትን ሱዳን ያቀረበችውን ሰነድ መልሰው ተቃውመዋል።
በተጨማሪም የራሳቸውን አቋም ይዘው እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን የተቃወሙት ግብፃውያኑ ተደራዳሪዎች ፣ ድርድሩ እየተካሄደ የግድቡ ውሃ ሙሌት ሊካሄድ አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።
እንደዚሁም እየተካደ ያለው ድርድር ሰኞ እንዲጠናቀቅ እና እስካሁን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያስቀመጧቸውን በድርድሩ ለተገኙ ለውጦች እውቅና ላለመስጠት ፍላጎት ታይቶባቸዋል ነው ያለው።
ድርድሩ ዛሬም እንደሚቀጥል የጠቆመው ሚኒስቴሩ የተደረጉ ድርድሮችን መሰረት በማድረግ በተዘጋጁ መመሪያዎች እና ህጎች ላይ ሀሳብ ይለዋወጣሉ ብሏል።
ነገ ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም በእስካሁኑ ድርድር የተገኙ ለውጦችን በመገምገም ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በግብጽ ሊቀመንበርነት ድርድሩ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማደናገር እና በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሰደር የሚደረግ ማንኛውም ዘመቻ ወይም ኢትዮጵያ ያልተካተተችበትን በቅኝ ግዛት ላይ የተመሰረቱ ስምምነቶችን እንድትቀበል በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም ሲል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢፌዴሪ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ እ.ኤ.አ. ሰኔ 13 ቀን 2020 የግብጽ የውሃ ሀብትና የመስኖ ልማት ቃል አቀባይ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳዘነውም ነው የገለጸው፡፡ ቃል አቀባዩ በመግለጫው “ድርድሩ በኢትዮጵያ ምክንያት እየተበላሸ ነው” የሚል ክስ ቢሰነዘርም ፣ እውነታው ግን በድርድሩ ለውጥ እያመጣን መሆኑ ሲሆን ቀጣይ ድርድሩ መሰናክል ቢገጥመው እንኳን ግብፅ በቅኝ ግዛት ላይ የተመሠረተ የውሃ ስምምነትን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ነው ሲልም መግለጫው ያትታል፡፡ የቅኝ ግዛቱ ስምምነት የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ እና ህጋዊ መብቶቻቸውን የሚደፈጥጥ እንደሆነም ሚኒስቴሩ አስታውሷል፡፡
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛለች፡፡
ከግድቡ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ዉጥረት እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድርድሩ እንዲቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው ዉይይት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው ድርድሩ በድጋሚ መካሔድ የጀመረው፡፡