ኢትዮጵያ ግብጽ ኃላፊነት ከጎደለው መግለጫዎቿና ማስፈራሪዎቿ እንድትታቀብ አሳሰበች
ግብጽ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ "ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው" ማለቷን ኃላፊነት የጎደለው ነው ስትል ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋለች
ኢትዮጵያ “ግብጽ በማስፈራራትና በህገ ወጥ ተግባራት ፍላጎቷን ማሳካት አትችልም” ብላለች
ኢትዮጵያ ግብጽ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኃላፊነት ከጎደለው መግለጫዎቿና ማስፈራሪዎቿ እንድትታቀብ አሳሰበች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኃላፊነት የጎደለው ማስፈራሪያ የታከለበት መግለጫዎችን እያወጣ ነው ብሏል።
በተለይም የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ "ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው" በማለት የሰጡትን መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውድቅ አድርጎታል።
- ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባሰለፈው ውሳኔ ማዘኗን ገለጸች
- ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ህጋዊ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ጥሪ አቀረቡ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የግብጽ ተግባር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር እና የአፍሪካ ህብረት ድንጋጌን በግልጽ የሚጥስ መሆኑን ሲልም ገልጿል።
ተግባሩ እራሷ ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ጋር በፈረንጆኑ 2015 ላይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የፈረመችውን የመርህ ስምምነት የሚጥስ ተግባር እየፈጸመች መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል።
የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ አካላት ግብጽ የዓለም አቀፉ ግንኙነት ደንብን እየጣሰች መሆኗን ልብ ሊሉ ይገባል ያለችው ኢትዮጵያ፤ ግብጽ ተገቢ ያልሆኑና ህገወጥ መግለጫዎችን ከማውጣት እንድትቆጠብ አሳስባለች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አክሎም፤ ግብጽ በማስፈራራትና ከህግ ውጭ ነገሮችን በማድረግ ፍላጎቷን ልታሳካ እንደማትችልም አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ ሁሉም ወገኖች በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ወደሚደረገው ንግግር እና ድርድር እንዲመለሱም ጥሪ ያቀረበች ሲሆን፤ ሁሉም ወገን እኩል ተጠቃሚ በሚያደርግ አቋማ የጸናች መሆነኗንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።