ግብጽ ኢትዮጵያ እና ራስገዟ ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት እንደማትደግፍ መግለጿ ይታወሳል
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስመራ ገቡ።
የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜይ ሽኩሪ ኤርትራ ገብተዋል።
ሚንስትሩ ወደ አስመራ ያቀኑት የፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲን መልዕክት ይዘው እንደሆነ ተገልጿል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ኤርትራ አምርተው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ይህን ተከትሎም ግብጽን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት የሱማሊያ ሉዓላዊነትን እንደሚያከብሩ ስምምነቱን እንደማይደግፉት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የፈረሙት ስምምነት የሚጎዳው ሀገርም ሆነ የሚጥሰው ህግ እንደሌለ ገልጿል።
መንግስት ኢትዮጵያ ለባህር ኃይል የሚሆን የጦር ሰፈር ስታገኝ፣ ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምታገኝ ተስማምቷል።
መንግስት ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠትን በተመለከተ ኢትዮጵያ አጢና አቋም ትወስዳለች ብሏል።