በዉጭ ሀገራት የሚደገፉት የሊቢያ 2 ተቀናቃኞች ፍልሚያ ሀገሪቱን የእጅ አዙር ጦርነት ማዕከል እንዳያደርጋት ተሰግቷል
የቱርክና ግብጽ ፍጥጫ በሊቢያ
ከሞሐመድ ጋዳፊ መገደል በኋላ ሊቢያ እደቀድሞዋ መሆን ተስኗት የራሷ ጉዳይ በውጭ ኃይሎች ላይ ከወደቀ ሰነባብቷል፡፡ ጎረቤቷን ግብጽን ጨምሮ ቱርክ ፣ ሩሲያ ፣ ሳዑዲ አረቢያ ፣ ኳታር ፣ ፈረንሳይና ሌሎችም በሊቢያ ጉዳይ ያገባናል ባይ ናቸው፡፡ በትሪፖሊና በምስራቃዊ ሊቢያ የተከፋፈሉ መንግስታትም የሊቢያን ህዝብ “ለኔ ገብር ለኔ” እያሉት ናችው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው ብሔራዊ የስምምነት መንግስትና በጄነራል ካሊፋ ሃፍታር የሚመራው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ሀገሪቱን እያመሷት ስለመሆኑ መገናኛ ብዙሃ እየጻፉ ነው፡፡ ጀሩሳሌም ፖስት የተባለው ጋዜጣ አሁን ላይ ቱርክ በሊቢያ ጉዳይ ጡንቻዋን እያሳየች ነው ሲል ጽፏል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የካሊፋ ሃፍታር ጦር የትሪፖሊን አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠሩ ተገልጾ ነበር፡፡ ይሁንና በቱርክ የሚደገፈው የትሪፖሊው መንግስት በከፈተው ዘመቻ አውሮፕላን ማረፊያውን ዳግም በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ ይታወሳል፡፡
በሊቢያ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ ሩሲያና ቱርክ ጥረት ማድረጋው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁንና የፋይዝ አልሳራጅ እና የካሊፋ ሃፍታር መንግስታት ጦርነቱን አቁሞ ከመሸማገል ይልቅ በየፊናቸው ደጋዎቻቸውን በማሰባሰብ መዋጋትን መርጠዋል፡፡
የካሊፋ ሃፍታርን ጦር ከሚደግፉት መካከል አንዷ የሊቢያ ጎረቤት ግብጽ ናት፡፡ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ የአየር ሃይላቸው በተጠንቀቅ እንዲቆምና የሊቢያን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተል ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡ ቱርክ ደግሞ በምክር ቤቷ ጭምር ወታደሮችን ወደ ሊቢያ ለመላክ መወሰኗ ይታወሳል፡፡ እናም የሊቢያ ጉዳይ ሁለቱን ሀገራት ወደ መካረር ያስገባ መሆኑን ተንታኞች ገልጸዋል፡፡
አንካራ አሁን ላይ በሜዲተራኒያን ባህር ዳርቻ ከፍተኛ ቁጥጥር ለማድረግ ማሰቧን እየገለጸች ነው፡፡ ግሪክና ቆጵሮስን ወደ ሜዲተራኒያን ባህር እንዳይገናኙ የሚያደርግ ካርታም ማዘጋጀቷ ነው የተሰማው፡፡ በባህሩ አካባቢ ያለውን ሃብትም ቱርክ መቆጣጠር ትፈልጋለች የሚሉ ሃሳቦችም ተሰምተዋል፡፡
በሊቢያ ያለው ሁኔታ በጣም የተወሳሰብ ነው የሚለው ጀሩሳሌም ፖስት በሀገሪቱ የሚካሄድ የእጅ አዙር ጦርነት በዋናነት ሀገሪቱን ሰላም በማሳጣት ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡
ለዚህ ማሳያው ደግሞ ግብጽ ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲቆም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መግለጻቸው እንዲሁም ቱርክ ኤስ 400 መሳሪያዎችን ከሩሲያ መግዛቷ ነው፡፡ አንካራ በተደጋጋሚ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ሊቢያ ማምጣቷን መቀጠሏም በሊቢያ ያለው ሽኩቻ እየጨመረ መምጣቱን ያመለክታል፡፡
የሃፍታር ደጋፊ ግብጽ ከሰሞኑ የጦርነት ጉሰማ ስታሰማ ቱርክ ደግሞ ተኩስ አቁም ሊደረግ ይገባል እያለች ነው፡፡ በተደጋጋሚ ተኩስ አቁም ይኑር የምትለው አንካራ ይህ ግን ራሱን የሊቢያ ጦር ብሎ በሰየመው የካሊፋ ሃፍታር ጦር ሲደናቀፍ ስለመቆየቱ ይነሳል፡፡
የቱርክ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ኢብራሂም ካሊን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሃፍታር ጦር ሲርጥና ጁፍራን መልቀቅ አለበት ብለዋል፡፡ ሁሉም ወደ 2015 ይዞታ ከመጣ የታለመው የተኩስ አቁም ጉዳይ ሊሳካ እንደሚችልም ቃል አቀባዩ ስለመናገራቸው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ቱርክ በተባበሩት መንግስታት ዕውቅና ላለው የፋይዝ አልሳራጅ መንግስት ድጋፏን እንደምታጠናክር የገለጹት ቃል አቀባዩ ኢብራሂም ካሊን የሊቢያ መንግስት ቱርክን እስከፈለገ ድረስ በስፍራው እንቆያለን ብለዋል፡፡
ካሊፋ ሃፍታር ሁሉንም የተኩስ አቁም ስምምነቶች መጣሱን የገለጹት ቃል አቀባዩ ግብጽ ሃፍታርን መደገፏ የተሳሳተ ፖሊሲ መከተሏን ያሳያል ብለዋል፡፡
ትናንት ግብጽ ጦሯን እንዲዘጋጅ ማዘዟ የተሰማ ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁን ካሊፋ ሃፍታርም ፋይዝ አልሳራጅም ድጋፍ እያገኙ ናቸውና የጦርነት ጉሰማው አልቆመም፡፡ምናልባትም በቀጣይ በሊቢያ የውጭ ኃይሎች በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር ወደ ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ ግምቶች ተቀምጠዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እውን በሊቢያ ጉዳይ ካይሮና አንካራ ይዋጉ ይሆን የሚሉ ጥያቄ አዘል ሀሳቦችን እየሰነዘሩ ነው፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን በሊቢያ በሁለት ጎራዎች እየተታኮሱ ያሉት በውጭ ኃይሎች የታገዙ ናቸው፡፡