የዩክሬን ዛፖሪዝሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ስራውን ማቁሙ ተገለጸ
ተመድ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አከባቢ ከጦር ነጻ እንዲሆን ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው
የዩክሬን ብሔራዊ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ኢጀንሲ ጣቢያው ስራው እንዲቆም የተደረገው ለደህንነት ሲባል ነው ብሏል
በዩክሬን ውስጥ በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የዛፖሪዝያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ስራው ማቆሙ የዩክሬን ብሔራዊ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ኢጀንሲ(ኢነርጎአቶም) አስታወቀ፡፡
የኒውክሌር ጣቢያው ስራው እንዲቆም የተደረገው ለደህንነት ሲባል ነው ያለው ኤጀንሲው፤ አሁን ላይ የሩሲያ ኃይሎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ቁጥር 6 የኃይል ዩኒት ከአውታረ መረቡ ያለው መስመር መቋረጡንም ገልጿል፡፡
ባለው ሁኔታ በመስመሩ ላይ ተጨማሪ ጉዳት የመድረስ እድሉ ከፍተኛ ነው ሲልም ያለው ስጋት ኢጄንሲው መግለጹም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ በጦርነቱ ምክንያት በአከባቢው ላይ መጠነ ሰፊ የተኩስ ልውጦች እየተካሄዱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፤ በጣቢያው ላይ ጥቃት ከደረሰ የጨረር አደጋ እንዳያስከትል በርካቶች ስጋታቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ዩክሬን፤ የሩሲያ ኃይሎች በኒውክሌር ጣብያው ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ስትል ክስ ማቅረቧ የሚታወስ ነው፡፡
ከዛም አለፍ ብሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በቅረቡ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “አሁን ዓለም አንድን የኒውክሌር ሃይል ጣቢያ ለመከላከል ጥንካሬ እና ቆራጥነት ካላሳየ ተሸንፏል ማለት ነው፤ ለኒውክሌር ጥቃት እጁን ይሰጣል” በማለት በኒውክሌር ጣቢያው ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ያለው ትርጉም ግዙፍ መሆኑ ሲናገሩ ተሰምቷል።
ሩሲያ በበኩሏ የዩክሬን ጦር ግዙፉን የኒውክሌር ጣቢያ ለማውደም ተኩስ ከፍተዋል በማለት ኪቭን ስትከስ ተደምጣለች።
ሞስኮ፤ ዩክሬን ግዙፉን አቶሚክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ማውደሟ “አሰቃቂ መዘዝ” ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ልታውቅ ይገባል ስትል አማስጠንቀቋም ጭምር አይዘነጋም።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የዩክሬን ታጣቂ ሃይሎች የኒውክሌር ጣቢያን ማውደም ከዩክሬን ባለፈ ለአውሮፓ ምድር እጅግ አደገኛ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው”ሲሉም ነበር የተደመጡት ከሶስት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ፡፡
በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተስግቷል።
በዚህም ሁኔታው ያሰጋው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አከባቢ ከጦር ነጻ እንዲሆን ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ሁለቱም አካላት የኃይል ጣቢያው አካባቢ ውጊያ እንዲያቆሙ መጠየቁም እንዲሁ አይዘነጋም፡፡
አሜሪካም ብትሆን ቦታው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆንና ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቦታውንና አከባቢው ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቀሴ አሳስባ ነበር፡፡
በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ አቶሚክ ሃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡