ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የአሜሪካ ቪዛ ሲጠይቁ የቆዩት የሩሲያ ልዑካን ወደ ኒውዮርክ ለመሄድ የሚያስችል ቪዛ አገኙ
ሩሲያ ቪዛው ከመዘግየቱ ጋር በተያያዘ “አሜሪካ ግዴታዎቿ እየጣሰች ነው” የሚል ክስ ስታቀርብ መቆየቷ አይዘነጋም
አንጋፋው ዲፕሎማት ሰርጌ ላቭሮቭ “በፑቲን ምትክ በጠቅላላ ጉባዔው ሩሲያን ወክለው በመሳተፍ ላይ ናቸው” ተብሏል
ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ የአሜሪካ ቪዛ ሲጠይቁ የቆዩት የሩሲያ ልዑካን ወደ ኒውዮርክ ለመሳተፍ የሚያችላቸው ቪዛ አግኝተዋል፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና የሩሲያ ልዑካን ቡድን አባላት በኒውዮርኩ ስብሰባ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ቪዛ ማግኘታቸው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሩሲያ፤ 77 ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ለሚወክላት ልዑክ የቪዛ ጥያቄ ማቅረቧን ካቀረበች ብትቆይም አሁን ላይ የዘገየ ምላሽ ማግኘቷ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ሞስኮ፤ አሜሪካ በጠቅላላ ጉባኤው ሙሉ በሙሉ የሩሲያ ተሳትፎን ለመከላከል እየሞከረች ነው የሚል ክስ ስታሰማ መቆየቷም አይዘነጋም፡፡
“አሜሪካ ግዴታዎቿ እየጣሰች ነው” ሲሉም ነበር የከሬምሊን ሰዎች ዋሽንግተንን የወቀሱት፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዘንድሮ በሚካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደማይገኙ ቀድመው መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህ መሰረት በጉባዔው ሩሲያን የሚወክሉት ከፑቲን ቀጥሎ ወዳጆቻቸው “ጠንካራው ዲፕሎማት” የሚሏቸው፤ ምዕራባውያን ደግሞ “አደገኛው” የሚሏቸው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሩቁ ሰርጌ ላቭሮቭ ሆነዋል።
ሰርጌ ላቭሮቭ የሀገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2004 ነበር። የ77 ዓመቱ ሰርጌ ላቭሮቭ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት ለ10 ዓመታት ማለትም ከአውሮፓውያኑ 1994 እስከ 2004 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ቋሚ መልዕክተኛ ነበሩ።
ሩሲያን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 77 ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የወከሉት ሰርጌ ላቭሮቭ በሀገራቸው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መስራት የጀመሩት በ22 ዓመታቸው ሲሆን በድምሩ ለግማሽ ክፍለ ዘመን (ለ 50 ዓመታት) ያገለገሉም ናቸው።
77 ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በፈረንጆቹ ከዛሬ መስከረም 13 እስከ 20 በኒውዮርክ እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።