የግብጽ ጦር ወታደሮቹ ሱዳንን ለቀው እንደወጡ እስካሁን አላሳወቀም
የሱዳን ጦር በሀገሪቱ የነበሩ 200 ገደማ የግብጽ ወታደሮችን ወደ ግብጽ ማስወጣቱን አስታውቋል።
የሱዳን ጦር እንዳስታወቀው 177 የግብጽ አየር ኃይል ወታደሮች በሰሜናዊ ሱዳን ሜሮዌ ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱ ተይዘው ከቆዩ በኋላ ወደ ግብጽ ተወስደዋል።
የሱዳን ጦር ባወጣው መግለጫ ግብጻውያኑ በአራት የካይሮ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከሰሜናዊቷ ዶንጎላ ከተማ እንዲወጡ ተደርጓል ብሏል።
ጦሩ እንዳለው የግብጽ ወታደሮች በጋራ የአየር ኃይል ልምምድ ለመሳተፍ በሱዳን ነበሩ መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የግብጽ ጦር ወታደሮቹ ለቀው እንደወጡ ባያሳውቅም፤ ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ ወታደሮቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር በማስተባበር ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ባለፈው ቅዳሜ በሱዳን አር.ኤስ.ኤፍ በሚባለው ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት እና በሀገሪቱ ጦር መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ፤ በሀገራቱ ድንበር በቅርብ እርቀት ላይ በምትገኘው ሜሮዌ ከተማ የግብጽ ወታደሮች "ተይዘዋል" ተብሏል።
“ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ተብሎ የሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ባሳለፍነው ቅዳሜ ጠዋት በካርቱም ውስጥ የግብጽ ወታደሮችን ማግኘቱን አስታውቆ ነበረ።
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ በሰጡት ማብራሪያ ሱዳን ውስጥ ያለው የሀገሪቱ ሰራዊት ለጋራ ወታደራዊ ልምምድ ወደ ካርቱም ያቀኑ መሆኑን እና ለየትኛውም ወገን ድጋፍ የማይሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በሱዳን ውስጥ ያሉ የግብጽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ደህንነትን ለማረጋገጥ ግንኙነቶችን እያደረገን ነው ሲሉም ገልጸው ነበር።