ግብጽ በሱዳን ያለው ሰራዊቷ ለወታደራዊ ልምምድ ተልእኮ ወደ ካርቱም ያቀና መሆኑን አስታወቀች
የሱዳን ፈጠኖ ደራሽ በካርቱም ውስጥ የግብጽ ሰራዊትን እንደያዘ ማሳወቁ ይታወሳል
በሱዳን ያለው የግብጽ ሰራዊት የትኛውንም ወገን እንደማይደግፍ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ገልጸዋል
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ሱዳን ውስጥ ያሉት የሀገሪቱ የጦር ሰራዊት አባላት ለጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተልእኮ ወደዛ ያቀኑ እንደሆነ አስታወቁ።
“ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ተብሎ የሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ባሳለፍነው ቅዳሜ ጠዋት በካርቱም ውስጥ የግብጽ ወታደሮችን ማግኘቱን አስታውቆ ነበረ።
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ በሰጡት ማብራሪያ ሱዳን ውስጥ ያለው የሀገሪቱ ሰራዊት ለጋራ ወታደራዊ ልምምድ ወደ ካርቱም ያቀኑ መሆኑን እና ለየትኛውም ወገን ድጋፍ የማይሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በሱዳን ውስጥ ያሉ የግብጽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ደህንነትን ለማረጋገጥ ግንኙነቶችን እያደረገን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ከግብጽ ጦር ማእከላዊ ምክ ቤት አባላት ጋር ትንናት ሰኞ ባደረጉት ውይይት ላይ ፤ “በሱዳን እየተካሄደ ያለው የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ለማሸማገል ዝግጁ ነን” ብለዋል።
በሱዳን እየተዋጉ ያሉ አካላት ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ቢፊቱ መልካም እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
“ከሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እያደረገን ነው” ያሉት ፐሬዝዳን አል ሲሲ “የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ድርድር እንዲጀመር እየተነጋገርን ነው” ማለታቸውም ተግልጿል።
በሱዳን ባሳለፍነው ቅዳሜ ጠዋት በሀገሪቱ መደበኛው የመከላከያ ሰራዊት እና “ራፒድ ሰፖርት ፎርስ (አር.ኤስ.ኤፍ)” ተብሎ የሚጠራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለ4ኛ ቀን ቀጥሏል።
በጦርነቱ 200 ገደማ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ ከ1ሺህ 400 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም እየተነገረ ይገኛል።