“የፌልትማንም ይሁን የኮንጎ ፕሬዚዳንት መምጣት የግድቡን ሙሌት አያስቀርም” አምባሳደር ዲና
ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘም የተቀየረ አቋም እንደሌለ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል
ቃል አቀባዩ በግድቡ ጉዳይ የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ብቻ ይመራ የሚለው “የኢትዮጵያ አቋም አይቀየርም” ብለዋል
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ስለመጡ “ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ የምትለውጠው አቋም የለም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ።
በግድቡ ጉዳይ የሚደረገውን ድርድር በተመለከተ የድርድሩ ሂደት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ብቻ ይሁን የሚለው የኢትዮጵያ አቋም ይቀጥላል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
“የፌልትማንም ይሁን የኮንጎ ፕሬዚዳንትም መምጣት ሙሌቱን አያስቀርም ፤ ሙሌቱ የግድቡ አካል ነው ፤ ይቀጥላል” ሲሉም ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ያስታወቁት።
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን እንዲሁም የዲ.አር. ኮንጎ ፕሬዝደንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ቼሲኬዲ ለስራ ጉብኝት በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡
የአውሮፓ ሕብረት ባለሙያ እልካለሁ ያለው ኢትዮጵያ አቋም ቀይራ ነው ወይ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ አምባሳደር ዲና ሲመልሱ “ምንም የተቀየረ አቋም የለም ፤ ምርጫውን ያዩታል” በማለት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሔድ አንስተዋል።
የአሜሪካው ልዩ ልዑክ ፌልትማን ፣ “የምርጫውን መተላለፍ በተመለከተ የኔ ስራ አይደለም ፤ የአሜሪካ መንግስት የላከኝ ለሱ አይደለም” ስለማለታቸውም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በሱዳን ዳርፉር የነበሩ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን የሰላም ማስከበር ተልዕኮው መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው አንመለስም ስለማለታቸው ፣ አምባሳደር ዲና መረጃ የለኝም ያሉ ሲሆን ነገር ግን “መመለስም አለመመለስም መብት ነው” ብለዋል፡፡