በጅማ እና በአማሮ የታጠቁ ሀይሎች በከፈቱት ተኩስ ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ጥቃቶች መደጋገማቸውንና መስፋፋታቸውን በማስታወስ የፀጥታ መዋቅሩ የመከላከልና ዝግጁነት አቅም ሊሻሻል እንደሚገባውም ነው ኮሚሽኑ ያሳሰበው
ኮሚሽኑ ከሰሞኑ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን እየተከታተለ መሆኑንም ገልጿል
ከሰሞኑ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን እየተከታተለ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ኢሰመኮ እንዳሳወቀው በጅማ እና አማሮ የታጠቁ ሀይሎች በከፈቱት ተኩስ ሰላማዊ ዜጎች ሞተዋል።
በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መደጋገማቸውንና መስፋፋታቸውን ያስታወሰው ኮሚሽኑ “የፀጥታ መዋቅሩ የመከላከልና ዝግጁነት አቅም ሊሻሻል” እንደሚገባ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ሊሙ ኮሳ ወረዳ ቀጮ ክርክራ እና ጋሌ ቀበሌ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ/ም በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት መድረሱን ገልጿል።
በተመሳሳይ በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ፣ ዳኖ ቀበሌ በሚያዚያ 14 ታጣቂዎች 6 ሰዎች እንደገደሉ የአካባቢው አስተዳደር ማሳወቁንም አስታውቋል።
በሁለቱ ክልሎች የተከሰቱትን የንጹሃን ዜጎች ግድያ እየተከታተለ እንደሚገኝ የገለጸም ሲሆን በኮሳ ወረዳ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በእለቱ የክልል እና የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን መረዳቱን አሳውቋል።
ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና ክልል አካላት ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ በቅርበት እየተነጋጋረ መሆኑ ገልጾ፤ የክትትል ተግባሩን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳትና የሰዎች ሞት ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ያሳሰበው ኮሚሽኑ በንጹሃን ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተደጋጋሚነት እና መስፋፋት የፀጥታ መዋቅሩ የመከላከል እና ዝግጁነት አቅም ከፍተኛ መሻሻል ሊደረግበት እንደሚገባ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።