ኢሰመኮ እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ በትግራይ በጋራ ስምሪት ሊያደርጉ ነው
የአክሱሙ ድርጊት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን እምደሚችል ኢሰመኮ መግለጹ ይታወሳል
የጋራ ስምሪቱ በቅርቡ እንደሚጀመር እና በመጀመሪያ ዙር ለሦስት ወራት እንደሚቆይ ተገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ፣ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ የጋራ ምርመራ ለማካሄድ መስማማታቸውን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ አካላት የሚያደርጉት ምርመራ ዋና አላማው የተፈጸሙ ወንጀሎችን በማጣራት ተጠያቂዎች ወደ ህግ ቀርበው ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብሏል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ ፣የጦርነቱ ተዋናዮች በርካታ እንደመሆናቸው የተከሰተውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማወቅ አስቸኳይ የገልተኛ አካል ማጣራት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በክልሉ የሚደረገው የጋራ ስምሪት በቅርቡ እንደሚጀመርና የመጀመርያ ሶስት ወራት ስራውን እንደሚያከናውንም ነው የኢሰመኮ መግለጫ ያስታወቀው፡፡
ኮሚሽኑ ከትናንት ወዲያ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ፣ በአክሱም ከተማ በተለይም ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበሩት ሁለት ቀናት "ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸመ" ይፋ አድርጓል። በአጠቃላይ ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።
የአክሱሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ስለሚችል በክልሉ የተሟላ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በተመለከተ ለሚደረገው ማጣራት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ስምምነት መደረሱን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊ ሚሼል ባሽሌት ከሳምንት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡