ኢሰመኮ፤ በወለጋ እና አካባቢው የተሰማሩ የመንግስት የጸጥታ አካላት የበለጠ እንዲጠናከሩ ጥሪ አቀረበ
ጠ/ሚ ዐቢይ በቄለም ወለጋ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ እንደተፈጸመባቸው ትናንት መግለጻቸው ይታወሳል
ኢሰመኮ "ማንነት ላይ ያነጣጠረው ግድያ በአስቸኳይ መቆም" እንዳለበት አሳስቧል
ኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገው የዜጎች ግድያ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ ትናንት ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ/ም በቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ መንደር 20 እና 21 ተብለው በሚጠሩ መንደሮች በሚኖሩ አማራዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እንደደረሱት ገልጿል፡፡
የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ እና ስለ ግድያው ለመረዳት ከግድያው ተርፈው ከአካባቢው የሸሹ ሰለባዎችንና የአካባቢውን ነዋሪዎች እየጠየቀ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ ትናንት ጠዋት ቀደም ብሎ መፈጸም የጀመረው ግድያ በኦነግ ሸኔ አባላት መፈጸሙን ነግረውኛል ብሏል፡፡
ግድያው ከማለዳ 11፡00 ጀምሮ መፈጸሙን ከግድያው የተረፉ የጥቃቱ ሰለባዎች ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
የመንግስት የጸጥታ አካላት በስፍራው ቢደርሱም በሌሎች አካባቢዎች መጠለላቸውንም ነው ነዋሪዎቹ ለኮሚሽኑ የገለጹት፡፡
በስፍራው እየደረሰ ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ ያሳሰቡት ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) በአካባቢው የተሰማሩ የመንግስት የጸጥታ አካላት ግድያውን ማስቆም በሚያስችል መልኩ እንዲጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ እንደተፈጸመባቸው ትናንት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በመግለጫው ምን ያህል ዜጎች እንደተጨፈጨፉ ባይገልጹም፤ "የጸጥታ አካላት ከሚያደርሱበት ዱላ የፈረጠጠው የሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋ በዜጎች ላይ አደጋ እያደረሰ በመሸሽ ላይ ነው" ብለዋል ግድያውን በፈጸመው አሸባሪ ቡድን ላይ እስከመጨረሻው ክትትል ተደርጎ እንደሚወገድ በመጠቆም።
ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉ በግድያው ማዘኑን ገልጾ ድርጊቱን ያወገዘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "አሸባሪው የሸኔ ቡድን በጸጥታ ሀይላችን በከፍተኛ ሁኔታ ጥቃት እየደረሰበት በመሆኑ ከጥቃቱ በመሸሽ" ላይ መሆኑን ገልጿል ግድያው በዛ ምክንያት ማጋጠሙን በመግለጽ፡፡
"ከጸጥታ ሀይላችን ጋር በመተባበር እስከመጨረሻው እናስወግደው" ሲልም ጥሪ አቅርቧል ምክር ቤቱ።
ሽሽት ላይ ስለመሆኑ የሚነገርለት አሸባሪው ቡድን ባሳለፍነው ሳምንትም (እሁድ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ/ም) በጊምቢ ወረዳ በሚገኙ ቶሌ እና ሌሎችም ቀበሌዎች በፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ 338 አማራዎች እንደተገደሉ መገለጹ የርታወሳል፡፡
ሆኖም በሳምንቱ ጥቃቱ የተገደሉ ዜጎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ነው የሚነገረው፡፡ ተመድን መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማትም ድርጊቱ በገለልተኛ አካል እንዲጠናና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡
ግድያውን በተመለከተ አጣሪ ኮሚቴዎችን ያዘጋጀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ በአጀንዳነት እንዲያዝና የሃዘን ቀን እንዲታወጅ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል መቅረቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡