ኢሰመኮ “የጸጥታ ሀይሎች የሲቭል ሰዎችን ደህንነት” እንዲጠብቁ ጥሪ አቀረበ
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ግጭት አምርቷል
ኢሰመኮ “…የትግራይ ክልል የፀጥታ ሁኔታ የሚያሳስበው ሲሆን፣ ክስተቱን በቅርበት እየተከታተለው” መሆኑን አስታውቋል
ኢሰመኮ “…የትግራይ ክልል የፀጥታ ሁኔታ የሚያሳስበው ሲሆን፣ ክስተቱን በቅርበት እየተከታተለው” መሆኑን አስታውቋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ ዋና ኮሚሽነር ዳኒኤል በቀለ የፌደራል የክልል የጸጥታ ሃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁና ሰብአዊ መብትን እንዳይጥሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስትያ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ኢቲቪ ቀርበው ትግራይ ክልልን የሚመራው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሷል፤እርምጃም እንወስዳላን ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ ሁለቱ ወገኖች ወደ ግልጽ ግጭት ገብተዋል፡፡
የትግራይ ክልል በበኩሉ በትናንትናው እለት በክልሉ አዋሳኝ አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የአየር በረራም ማገዱን አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ በትግራይ ክልል “በፍጥነት እየተባባሰ የቆየውን የትግራይ ክልል የፀጥታ ሁኔታ የሚያሳስበው ሲሆን፣ ክስተቱን በቅርበት እየተከታተለው” መሆኑን ገልጿል፡፡
ኮሚሽነር ዳኒኤል በትግራይ ክልል“በበዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች” የሚያስጠልልም ስለሆነ ምግብና መድኃኒትና ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት፤ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም በማለት ምርጫ እንዲራዘም ሲያደርግ፣ህወሓት በራሱ ክልልዊ ምርጫ አድርጎ ነበር፡፡
ህወሓት የፌደራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ ሲገባው ከህገመንግስቱ ውጭ ነው ስልጣን ላይ ያለው ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ የህወሓት ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጋር ህጋዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው አለመግባባት ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ሊያመራ ችሏል፡፡