በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሰ መሄዱን ኢሰመኮ ገለጸ
በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ችግሮቹን የሚመጥን የመፍትሔ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም ተብሏል
ኢሰመኮ በኢትዮጵያ አስገድዶ መሰወር፣ በግዳጅ ማፈናቀል እና የዘፈቀደ እስር እንዳለ አስታውቋል
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሰ መሄዱን ኢሰመኮ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የ2015 ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
- ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረገች
- በኢትዮጵያ ሰዎችን አስገድዶ መሰወር አሳሳቢ መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በዚህ ጊዜ እንዳሉት "በኢትዮጵያ በ2015 ዓመት የሰላም ስምምነት እና የሽግግር ፍትህ ትግበራ ቢጀመርም ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አደጋ ውስጥ ነው" ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ የጸጥታ አካላት ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
ነገር ግን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀጥሏል ያሉት ዶክተር ዳንኤል የታጠቁ ሀይሎች አሁንም የዜጎች ስጋት መሆናቸው እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ታጣቂዎች ላይ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ሌላኛው የሰብዓዊ መብት ስጋት መሆኑም ተጠቅሷል።
ዶክተር ዳንኤል አክለውም መንግሥት ከታጠቁ ሀይሎች ጋር የጀመራቸውን የሰላም ውይይቶች እንዲቀጥልበት ያሳሰቡት ዶክተር ዳንኤል ይህ ሲሆን አደጋ ውስጥ የወደቀው የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት መፍትሄ እያገኘ እንደሚመጣ ተናግረዋል ።
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው በጸጥታ ሀይሎች አማካኝነት አሁንም በሰላም መንቀሳቀስ እንዳልተቻለ፣ ሰዎች ለእንግልት፣ ለአስገድዶ መሰወር፣ለጅምላ እስር መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በአንጻራዊነት የከፋ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
በሸገር ከተማ ገላን ከተማ ባለ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ካምፕ ውስጥ ዜጎችን ለረጅም ጊዜ ማሰር፣ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ተገደው እንዲያምኑ ማድረግ፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ማሰር እና ማዋከብ ይፈጸም እንደነበርም ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል።
እንዲሁም ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ በተወሰኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ገደብ መጣሉ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብትን እየጣሰ ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ እስር፣ ወከባ እና እንግልት መፈጸሙን እንደቀጠለ ነው ሲሉም ዶክተር ዳንኤል በመግለጫው ላይ ጠቅሰዋል ።
የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ታጠርጣሪዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እና ተጎጂዎችን ለመካስ በሚል የተጀመረው የሽግግር ፍትህ ስራ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አሳታፊ እና ሙያዊ ስነ ምግባርን በተከተለ መንገድ እንዲከናወን ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
ዶክተር ዳንኤል አክለውም የግጭት አፈታት እና የሰላም ድርድር ከታጠቁ ሀይሎች ጋር የተጀመረው ጥረት ሴቶችን ባሳተፈ መንገድ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።
ዓመቱ በአጠቃላይ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን የሚያስቀሩ ስራዎች ያልተሰሩበት ዓመት እንደነበር ኢሰመኮ ገልጿል።