በደብረ ኤልያስ ሁለት ገዳማት ከጥር ወር ጀምሮ ንጹሃን መገደላቸውን ኢሰመጉ አስታወቀ
በአካባቢው 'ታጣቂዎች እየሰለጠኑ ነው' በሚል በተጀመረው ግጭት ጉዳት መድረሱ ተነገረ
መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ተጠይቋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ግንቦት 28፤ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሦስት ክልሎችን ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁኔታ አሳውቋል።
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በሁለት ገዳማት "በአካባቢዉ የታጠቀ ቡድን እየሰለጠነ ነዉ" በሚል ከጥር 22፤ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረ ግጭት በንጹሃን ላይ ግድያና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
- ልዩ ኃይል እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ
- በአማራ ክልል መከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በብሄረ ብጹዓን አጼ መልክዓ ስላሴ እና ተክለ ኃይማኖት ገዳማት ከግንቦት 18፤ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የከባድ መሳሪያ ተኩስ መከፈቱን አስታውቋል።
በዚህም የአካባቢዉ አርሶ አደሮች በሰላም የግብርና ስራቸዉን ለመስራት እንደተቸገሩ እና የገዳማቱ መናኝ መነኩሴዎችም ላይ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን ገልጿል።
እንዲሁም ግጭቱን በሸሹ ሰዎች ላይ "ተምቻ" በተባለ ወንዝ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እየሆኑ ነው ሲል ኢሰመጉ ከአካባቢው አሰባሰብኩ ካለው መረጃዎች ተረድቻለሁ ብሏል።
መንግስት ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ በአካባቢው መሸጉ ያላችው ኃይሎች ትጥቅ ትግል ለማድግ ሲንቀሳቀሱ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል።
ከአምስት የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የተውጣጣው ግብረ ኃይል "በእስክንድር ነጋ" ይመራል ያለው ቡድን "መንግስትን ለመጣል" እቅድ እንዳለው ገልጿል።
ተወሰደ በተባለው እርምጃም 200 ታጣቂዎች መገደላቸውን ተናግሯል።
የታጣቂ ቡድኑን መሪና ግብረአበሮች እያሳደደ መሆኑን የገለጸው መንግስት፤ ስለ ንጹሃን ጉዳት ያለው ነገር የለም።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የፌደራሉ መንግስት ወደ አማራ ክልል ያሰገባውን ሰራዊት እንዲያስወጣ ጠይቋል።
የንቅናቄው ምክትል ሊቀ-መንበር መልካሙ ሹምዬ አሻም ለተባለ የግል የቴሌቪዥ እንደተናገሩት የሰራዊቱ መውጣት መግባባትንና መነጋገርን በመፍጠር መፍትሄውን ያቀላል።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በይፋ መፍረሱን ተከትሎ ክልሉ ለከፋ ቀውስና ትርምስ ተዳርጓል ያሉት ምክትል ሊቀ-መንበሩ ክልሉ "የጦር ቀጣና ሆኗል" ብለዋል።
የፌደራል መንግስት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይል አደረጃጀቶች እንዲፈርሱ መወሰኑን ተከትሎ የአማራ ልዩ ኃይል መፍረስ የለበትም የሚል ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል።
መንግስት ውሳኔውን በማይቀበሉት ላይ "የህግ ማስከበር" ስራ እንደጀመረም ገልጾ ነበር።
አብን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ የመንግስት ውሳኔ ሀገራዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ወሳኔው እንዲቀለበስ ጠይቆ ነበር።
ወሳኔው በሁሉም ክልሎች ላይ የማይተገበር እና የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት ያለመ ነው ሲል በጹኑ መቃወሙም ይታወሳል።