ኢሰመኮ በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ያሳስቡኛል አለ
ኢሰመኮ እንደገለጸው ይህ ግጭት የተከሰተው ሁለቱ ክልሎች ባለፈው ሚያዝያ ወር የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው
ኢሰመኮ የፌዴራል ባለስጣናት ጥረት አድርገው ግጭት እንዲያስቆሙ ጥሪ አድርጓል
ኢሰመኮ በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ያሳስቡኛል አለ።
በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የትጥቅ ግጭቶች፣ የንጹሃን ሞት እና መፈናቀል መኖሩን የሚያሳዩ ሪፖርቶች እንደሚያሳስቡት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ኢሰመኮ እንደገለጸው ይህ ግጭት የተከሰተው ሁለቱ ክልሎች ባለፈው ሚያዝያ ወር የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።
የንጹሃን ሞትን እና በግል እና በህዝብ ንብረት ላይ የደረሱ ውድመቶችን የተመለከቱ ቅሬታዎች እና ሪፖርቶች እየደረሱት መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ ከሳምንት በፊት ወደ ትጥቅ ግጭት ያመራው ውጥረት እየተባባሰ ነው ብሏል።
ኢሰመኮ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት መፈጠሩን እና በንጹሃን ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሎቹ የጸጥታ እና የአስተዳደር ባለስልጣናት እንዳረጋገጡለት ገልጿል።
ከዚህ በፊት በሁለቱ ክለሎች አዋሳኝ ቦታዎች በተቀሰቀሱ ግጭት በሁለቱም በኩል የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል።
ኢሰመኮ በመግለጫው በፌደራል የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት አማካኝነት ባለፈው ሚያዝያ ወር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ክልሎቹ የቆዩ ችግሮችን ለለፍታት ላደረጉት ጥረት እውቅና እንደሚሰጥም ገልጿል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ የፌዴራል ባለስጣናት ጥረት አድርገው ግጭት እንዲያስቆሙ ጥሪ አድርገዋል።
የፌደራል መንግስት በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሯል ስለተባለው ግጭት እስካሁን በይፋ ያለው የለም።
በኢትዮጵያ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ግጭቶችም እንደቀጠሉ ናቸው።
የፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎች በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች እና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም መንግስት "ሸኔ" ብሎ በሽብር ከፈረጀው ታጣቂ ቡድን ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
በተለይም በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር መንግስትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል።
ባለፈው አመት ሀምሌ ወር መጨረሻ በክልሉ እና እንደአስፈላጊነቱ በሌሎች አካባቢዎች ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሁለት ጊዜ ተራዝሞ ባለፈው ሳምንት ጊዜው አብቅቷል። ነገርግን መንግስት በይፋ አላነሳውም።
የአውርፓ ህብረት እና የአሜሪካ መንግስት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች በንግግር እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።