መንግስት በአፋር እና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ያለውን ግጭት እንዲፈታ ኢዜማ ጠየቀ
ሁለቱም ክልሎች ለችግሩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል
ኢዜማ ችግሩ የማይፈታ ከሆነ በሀገር ላይ ስጋት ይደቅናል ሲል አሳስቧል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፤ መንግስት በአዋሳኝ የአፋር እና የሱማሌ ክልል አካባቢዎች ያለውን ግጭት በዘላቂነት እንዲፈታ ጠየቀ።
ኢዜማ ችግሩ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብሏል።
የሁለቱም ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በመጠበቅ እና በሃገር ህልውና ላይ የተቃጣን ትንኮሳ በመመከት ታሪክ የሚያስታውሰው ገድል መፈጸማቸውን የገለጸው ኢዜማ ሲሆን ለችግሩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
"የክልሎቹ አመራሮች ከህወሓት እና አል ሸባብ በኩል የተሞከረባቸውን ጥቃት ለመመከት ባሳዩት ትዕግስት እና ቁርጠኝነት ልክ" በአዋሳኝ ቦታዎቹ ላይ በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ይስሩ ሲልም ነው ኢዜማ ጥሪ ያቀረበው፡፡
ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና በፈጠሩበት በዚህ ወቅት በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚገባው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ዜጎችን ለተጨማሪ የሰላም እጦትና የደኅንነት ችግር እንዲዳርግ መፈቀድ እንደሌለበትም ገልጿል።
ኢዜማ ጉዳቱ ከክልሎቹ አልፎ እንደ ሀገር ስጋት ከመሆን በተጨማሪ ለውጭ ሀይሎች መግቢያ ቀዳዳ እንደሚከፍት መረዳት ያስፈልጋልም ብሏል፡፡የፌደራሉ መንግሥትም የክልሎቹን ወቅታዊ ሁኔታ አስቸጋሪነት በመረዳትና ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ፓርቲው ጠይቋል፡፡