የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የ'ክላስተር' ክልል አደረጃጀትን ውድቅ አደረገ
ም/ቤቱ የ'ክላስተር' አደረጃጀትን 52 ለ 40 በሆነ አብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጓል
ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጉራጌ ዞን ከተሞች ሰሞኑን አድማ ተስተውሎ ነበር
በዛሬው እለት ስብሰባ ያደረገው የጉራጌ ዞን ም/ቤት የጉራጌ ዞን ከሌሎች ዞኖቾ ጋር በክላስተር እንዲደራጅ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አድርጓል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ መሐመድ ጀማል ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት፤ 52 የዞኑ ምክርቤት አባላት ጉራጌ ራሱን ችሎ በክልል ይደራጅ የሚለውን ሃሳብ ደግፈዋል።
የዞኑ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸካይ ጉባኤ፤ ከሌሎች የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር በክላስተር ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጓል።
የጉራጌ ዞንን በደቡብ ክልል ስር ከሚገኙ ሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በማዳመር የጋራ ክልል ለመመስረት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፤ 52 የምክር ቤት አባላት ተቃውመውታል።
40 የምክርቤት አባላት የክላስር አደረጃጀትን ደግፈዋል።
የክላስተር አደረጃጀቱን በአብላጫ ውድቅ ያደረገው ምክር ቤቱ፤ ጉዳዩ በህገመንግስቱ መሠረት እንዲታይ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል።
ሰሞኑን በጉራጌ ዞን በሚገኙ ከተሞች ከክልል እንሁን ጥያቄ ጋር በተየያዘ ስራ የማቆም አድማ ተደርጎ ነበር።
መንግስት ባቀረበው የ'ክላስተር' አደረጃጀት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት የጉራጌ ዞን የሚደራጀው ከስልጤ፣ ከየም ልዩ ወረዳ፣ከከንባታ ጠንባሮ እና ሀድያ ዞኖች ጋር ነው።
በደቡብ ክልል በርካታ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ሲነሱ የቆዩ ሲሆን በክልል ለመደራጀት ጥያቄ አቅርቦ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው ህዝበ ውሳኔ አማካኝነት ክልል የሆነው የሲዳማ ዞን ነው።