የጉራጌ ዞን፤ የክላስተር አደረጃጀት የተቃወመበትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ማስገባቱን አስታወቀ
የጉራጌ ዞንቤት ባለፈው ሃሙስ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የክላስተር አደረጃጀት በአብላጫ ድምጽ ተቃውሟል
የወረዳና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ጉባዔዎችን በተመለከተ የዞኑ አመራሮች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል
የጉራጌ ዞን፤ የዞኑ ምክር ቤቱን ከሰሞኑ ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ያሳለፈውን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባቱን አስታወቀ፡፡
የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሽያ አህመድ ዛሬ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የምክር ቤቱ ውሳኔና ተያያዥ ሰነዶች ለኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
የዞኑ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባደረገው ስብሰባ ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ያሳለፈውን ውሳኔ ዛሬ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባቱን ነው አፈጉባዔዋ የተናገሩት፡፡
አፈጉባዔዋ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ፤ የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ እንደሆኑ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ይህንን ደብዳቤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ባልደረቦች መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባልደረቦችም የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔን ለስራ ኃላፊዎች ማቅረባቸው እንደተገለጸላቸው አፈጉባዔዋ ጠቅሰዋል፡፡
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የገባው ሰነድ ሃሙስ ዕለት የዞኑ ምክር ቤት የክልል አደረጃጀትን በሚመለከት ያሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡
የዞኑ ምክር ቤት ሃሙስ ዕለት አድርጎት በነበረው አስቸኳይ ጉባዔ ከሌሎች ዞኖች እና ከአንድ ልዩ ወረዳ ጋር በክላስተርለመደራጀት የቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ በዚህ ውሳኔም 52 የምክር ቤት አባላት የክላስተር አደረጃጀትን ሲቃወሙ 40 አባላት ግን ደግፈውት ነበር፡፡
የዞኑ ምክር ቤት የክላስተር አደረጃጀትን ውድቅ ቢደርገውም በዞኑ የሚገኙ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ጉባዔዎችን በማድረግ ክላስተርን የሚደግፍ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡
ይህንን በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ጥያቄ ያቀረበላቸው አፈጉባዔ አርሽያ አህመድ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል፤ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ጉባዔዎችን በማድግ ክላስተርን የሚደግፍ ውሳኔ ማሳለፋቸውን በተመለከተ አል ዐይን ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበረ ቢሆንም አሁን መናገር እንደማይችሉና ጊዜው ሲደርስ አስተያየት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ከሀዲያ፤ ከስልጤ፣ ከከንባታ ጠንባሮና ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በክላስተር ተደራጅቶ ክልል እንዲሆን የሚል ምክረ ሃሳብ ቀርቦ ነበር፡፡