በጋምቤላ ክልል በነበረው ግጭት ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች መገደላቸው ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ገለጸ
ኮሚሽኑ በተፈጸመው ድርጊት ኦነግ ሸኔ፣ጋነግ፣ የክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች ተሳታፊ ነበሩ ብሏል
ኢሰመኮ በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ የፈጸሙ አካላት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲል አሳስቧል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ፣አካል ጉዳት እና ንብረት ዘረፋ የመሩ እያ ያስፈጸሙ አካላት በህግ ተጠያቂ ሊደረጉ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡
ግድያው የተፈጸመው በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ፣ም የክልሉ መንግስት ጸጥታ ሃይሎች በአንድ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በሌላ በኩል ሆነው ያደረጉትን ግጭት ተከትሎ መሆኑን ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡
የደረሰውን ጉዳት ከሰኔ 20-16 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ሲመረምር መቆየቱን የገለጸው ኢሰመኮ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂ ኃይሎች ላይ የወሰዷቸው እርምጃዎችን ተከትሎ በሲቪል ሰዎች ግድያ እና ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡
ኢሰመኮ በምርመራው “በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሳሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል” በሚል ምክንያት ሴቶችና የአእምሮ ህመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል፡፡
ግድያው በተናጠል እና በጅምላ መፈጸሙን የገለጸው ኢሰመኮ ከተገደሉት በተጨማሪ 25 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
በኦነግ ሸኔ፣ በጋነግ፣ በክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች በበርካታ ሰዎች ላይ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሟልም ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
በተኩስ ልውውጥ ወቅት በየትኛው አካል እንደተገደሉ ያልታወቀ 6 ሰዎች መሞታቸው የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲቪል ሰዎች አስክሬን በክልሉ ልዩ ኃይሎች እና መደበኛ ፖሊሶች በጭነት መኪና ተሰብስቦ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስዶ በጅምላ ተቀብሯል ብሏል፡፡
ኮሚሽኑአስክሬን እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ የሟች ቤተሰቦችም መከልከላቸውን ባገኘው መረጃና ማስረጃ እንዳረጋገጠ ገልጿል፡፡